ሃማስ በሰሜናዊ ጋዛ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዡ መገደሉን አስታወቀ
ከ2002 ጀምሮ የእስራኤልን ከሶስት በላይ የግድያ ሙከራዎች ያመለጠው አህመድ አል ጋንዱር የትና መቼ እንደተገደለ ግን አልተገለጸም
የእስራኤልና ሃማስ ተኩስ አቁም ስምምነት ሶስተኛ ቀኑን ይዟል
ሃማስ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዡ በሰሜናዊ ጋዛ መገደሉን ገለጸ።
የቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ አል ቃሳም ብርጌድ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ፥ አህመድ አል ጋንዱር የተባለው ወታደራዊ አዛዥ መገደሉን ይፋ አድርጓል።
አል ጋንዱር በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉ የሃማስ አመራሮች ሁሉ ከፍተኛውን ስልጣን የያዘ ስለመሆኑ ተገልጿል።
እስራኤል ከፈረንጆቹ 2002 ጀምሮ አል ጋንዱርን ለመግደል በጥቂቱ ሶስት ጊዜ ሙከራ ማድረጓን አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው አስታውሷል።
ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዡ መቼ እና የት እንደተገደለ የአል ቃሳም ብርጌድ መግለጫ አልጠቀሰም።
እስራኤልና ሃማስ ለአራት ቀናት ተኩስ ለማቆም የደረሱት ስምምነት ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን፥ የእስረኞች እና ታጋቾች ልውውጡም ቀጥሏል።
ከስምምነቱ በኋላ 248 ሰብአዊ ድጋፍ የጫኑ ተሽከርካሪዎችም ጋዛ መግባታቸውን የመንግስታቱ ድርጅት አስታውቋል።
11 አምቡላንሶች እና አልጋ ያላቸው ተሽከርካሪዎችም ለአል ሽፋ ሆስፒታል መሰጠታቸውንና ታጋቾችን ለማስለቀቅ የሚያግዙ ተሽከርካሪዎች መቅረባቸውንም ነው ተመድ የገለጸው።
ለአራት ቀናት የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነትን ተከትሎ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ለመመለስ ሲሞክሩ በእስራኤል ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል መባሉ በስምምነቱ ላይ ጥላ አጥልቶበታል።
ሃማስ ስምምነቱን እየጣሰች ነው በሚል እስራኤልን የወቀሰ ሲሆን፥ የእስረኞች ልውውጡ በትናንትናው እለት ለስአታት መስተጓጎሉም ይታወሳል።
ለጊዜውም ቢሆን ለጋዛ ነዋሪዎች እፎይታ የሰጠው የተኩስ አቁም ስምምነት ዘላቂ እንዲሆን አልያም ለቀናት እንዲራዘም የአለማቀፍ ሰብአዊ ድርጅቶች ጥሪያቸውን እያቀረቡ ነው።