ጋዛ የገቡት የእስራኤል እግረኛ ወታደሮች ድል እያደረጉ እንዳልሆነ ተገለጸ
እስራኤል ሐማስን ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ በሚል እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዛ ማስገባቷ ይታወሳል
በጋዛ የእግረኛ ጦር ውጊያ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከ110 በላይ የእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል
ጋዛ የገቡት የእስራኤል እግረኛ ወታደሮች ድል እያደረጉ እንዳልሆነ ተገለጸ
ለፍልስጤም ነጻነት እንደሚዋጋ የሚገልጸው ሀማስ ከ70 ቀናት በፊት በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ በአካባቢው ጦርነት ተቀስቅሷል።
ይህን ተከትሎም እስራኤል የአጸፋ እርምጃ የጀመረችው ዘመቻ አሁንም የቀጠለ ሲሆን እስካሁን 19 ሺህ ፍልስጤማዊያን እና ከ1 ሺህ 200 በላይ እስራኤላዊያን ተገድለዋል።
ሐማስን ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ በሚል ወደ ጋዛ የገባው የእስራኤል እግረኛ ጦር ያሰበውን ያህል ድል እያደረገ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡
ሮይተርስ የአይን እማኞችን ፣ የእስራኤል ጦርን እና ወታደራዊ ተመራማሪዎችን ዋቢ አድርጎ በሰራው ዘገባ የሐማስ ታጣቂዎች ከተገመተው በላይ ጠንካራ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
የእስራኤል ጦር አካባቢውን በሚገባ አለማወቁ፣ የሐማስ ታጣቂዎች ለዓመታት ሰፊ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸው እና ለረጅም ጊዜ ሊያዋጋቸው የሚችል የጦር መሳሪያ መያዛቸው ለእስራኤል እግረኛ ጦር ዋነኛ ፈተና እንደሆነበት ተገልጿል፡፡
በዚህም የሐማስ ታጣቂዎች በመሬት ውስጥ ለውስጥ ካዘጋጁት መጠለያ እየወጡ የእስራኤል እግረኛ ወታደሮችን እና የጦር ተሽከርካሪዎችን እየመቱ ነውም ተብሏል፡፡
ታጣቂዎቹ ሩሲያ እና ኢራን ሰራሽ የጦር መሳሪያዎችን በገፍ ከመታጠቃቸው ባለፈ በቀላሉ የሚሰሩ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን እንደታጠቁም ተገልጿል፡፡
እስራኤልን ኮንነው አስተያየት በመስጠት ላይ የነበሩ የቱርክ ፓርላማ አባል በልብ ህመም ህይወታቸው አለፈ
ለእስራኤል የቀጥታ የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማድረግ ላይ ያለችው አሜሪካ አሁን ላይ እስራኤል በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቃለች።
ፕሬዝዳንት ባይደን ከሰሞኑ ባደረጉት ንግግር እስራኤል ያላት ዓለም አቀፍ ድጋፍ እየቀነሰ ነው፣ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁም ነግሬዋለሁ ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ የዓለማች ሀገራት እስራኤል የተኩስ አቁም እንዲታወጅ ግፊት በማድረግ ላይ ሲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጦር ወንጀል እንዲጠየቁ በመወትወት ላይ ናቸው፡፡
እስራኤል በበኩሏ ከ70 ቀን በፊት በሐማስ ታግተው ከተወሰዱ ዜጎች ውስጥ 70 ዜጎች እስካሁን እንዳልተለቀቁ አስታውቃለች፡፡