የእስራኤል ልዩ ኃይል የታጋች አስከሬን ማግኘቱን ጦሩ አስታውቋል
የእስራኤል- ሀማስ ጦርነትን የተመለከቱ አዳዲስ ሁነቶች
በእስራኤል እና ሀማስ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ሁለት ወራት አልፎታል።
ሀማስ ድንበሯን ጥሶ ጥቃት የፈጸመባት እስራኤል እየወሰደችው ያለው መጠነሰፊ የአጸፋ ጥቃት 2.3 ሚሊዮን ነዋሪ ያላትን ጋዛን ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ከቷታል።
እስራኤል አሁንም ጥቃቷን ቀጥላበታለች።
የእስራኤል ልዩ ኃይል የታጋች አስከሬን አገኘ
የእስራኤል ልዩ ኃይል በጥቅምቱ ጥቃት የታገተችውን የ28 አመቷን ኢሊያ ቶሌዳኖ አስከሬን ማግኘት መቻሉን የእስራኤል ጦር ባወጣው
መግለጫ አስታውቋል።
ጦሩ እንደገለጸው በህክምና ባለስልጣናት አስፈላጊው የመለየት ሂደት መከናወኑን ገልጿል።
ቶሌዳኖ በደቡባዊ እስራኤል በተዘጋጀ የሙዚቃ ድግስ ላይ እየተሳተፈች ሳለ ነበር በሀማስ የታገተችው
አሁን ላይ በጋዛ 130 ሰዎች ታግተው እንደሚገኙ ይገመታል። የእስራኤል ባለስልጣናት የተወሰኑትን ሞተዋል ብለው አውጀዋል።
የአሜሪካ ለንጹሃን ጥበቃ ይደረግ የሚለው አዲስ ጥሪ
በተመድ የጸጥታው ምክርቤት የቀረበው የጋዛ የተኩስ አቁም የውሳኔ ሀሳብ ድምጽን በድምጽ የመሻር ወይም ቨቶ የማድረግ መብት ባላት አሜሪካ ተቃውሞ ሳይጸድቅ መቅረቱ ይታወሳል።
ይሁን እንጅ አሜሪካ ተኩስ አቁም እንዳይደረግ ብትቃወምም፣ እስራኤል በምታደርገው የማያባራ ጥቃት ንጹሃን እንዲጠበቁ እያሳሰበች ነው።
የአሜሪካ የደህንነት ልኡክ እስራኤል በሀማስ ላይ በምታደርገው ወታደራዊ ዘመቻ የስትራቴጂ ለውጥ በምታደርግበት ሁኔታ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
እስራኤል በሰሜን እና በደቡብ ጋዛ መጠነ ሰፊ የታንክ እና የአየር ድብደባ እያካሄደች ነው።
በካን ዮኒስ እና በራፋ በፈመችው ድብደባ ሁለት ህጻናትን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸውን የፍልስጤም ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ቱርክ ያወገዘችው የጀኒን ጥቃት
ቱርክ፣ የእስራኤል ኃይሎች በዌስት ባንክ ጀኒን ከተማ ወረራ በመፈጸም ያደረሱትን ጥቃት እና መስጊድ የማነወር ተግባር በጥብቅ እንደምታወግዝ የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ኦንሱ ከሲሊ የጀኒንን የስደተኞች ካምፕን ሰብሮ በመግባት የማምለኪያ ቦታን የመዳፈር ተግባር እንደሚያወግዙ ተናግረዋል።
የእስራኤል ወታደሮች ጀኒንን በወረሩበት ወቅት በሆስፒታል የነበረ ወጣት መግዳቸው እና በመስጊድ ውስጥ የጀዊሽ ጸሎት ማድረሳቸው ተገልጿል።
እስራኤል የዘመቻው አላማ ታጣቂዎችን ለመያዝ መሆኑን ብትገልጽም፣ የፍልስጤም ባለስልጣናት ግን 12 ሰዎች ተገድዋል ብለዋል።