እስራኤልን ኮንነው አስተያየት በመስጠት ላይ የነበሩ የቱርክ ፓርላማ አባል በልብ ህመም ህይወታቸው አለፈ
የፓርላማ አባሉ በሀይለ ቃል "እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው ስቃይ በአላህ መቀጣቷ አይቀርም" በማለት ላይ ሳሉ ተዝለፍልፈው ወድቀዋል
እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማዊያን 19 ሺህ ደርሷል
እስራኤልን ኮንነው አስተያየት በመስጠት ላይ የነበሩ የቱርክ ፓርላማ አባል በልብ ህመም ህይወታቸው አለፈ።
ለፍልስጤም ነጻነት እንደሚዋጋ የሚገልጸው ሀማስ ከ70 ቀናት በፊት በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ በአካባቢው ጦርነት ተቀስቅሷል።
ይህን ተከትሎም እስራኤል የአጸፋ እርምጃ የጀመረችው ዘመቻ አሁንም የቀጠለ ሲሆን እስካሁን 19 ሺህ ገደማ ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል።
የእስራኤል ጥቃት ራስን ከመከላከልም በላይ ነው በሚል ከበርካታ ሀገራት እና ተቋማት ተቃውሞ የገጠማት ሲሆን ከነዚህ መካከልም ቱርክ አንዷ ሀገር ነች።
ቱርክ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ ንጹሀንንን ኢላማ ያደረገ ጥቃት እንዲከፈት አድርገዋል በሚል በጦር ወንጀል እንዲጠየቁ በመወትወት ላይ ትገኛለች።
ከሰሞኑም የሀገሪቱ ምክር ቤት አባል የሆኑት ሀሰን ቢስሜት የተባሉ ግለሰብ በምክር ቤቱ ንግግር ማድረጊያ መድረክ ላይ ሆነው እስራኤልን እያወገዙ እያለ ተዝለፍልፈው መውደቃቸው በቀጥታ ስርጭት ላይ ተላልፏል።
እኝህ የምክር ቤት አባልም " እስራኤል በጋዛ ህጻናት ላይ እያደረሰችው ባለው ጥቃት ከአላህ ዋጋዋን ታገኛለች" እያሉ በሀይለ ቃል ሲናገሩ ተሰምቷል።
በንግግር መሀል ተዝለፍልፈው የወደቁት እኝህ የምክር ቤት አባል ወደ ሆስፒታል ለህክምና ቢወሰዱም ህይወታችው እንዳለፈ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።
ለእስራኤል የቀጥታ የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማድረግ ላይ ያለችው አሜሪካ አሁን ላይ እስራኤል በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቃለች።
ፕሬዝዳንት ባይደን ከሰሞኑ ባደረጉት ንግግር እስራኤል ያላት ዓለም አቀፍ ድጋፍ እየቀነሰ ነው፣ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁም ነግሬዋለሁ ብለዋል።