የሀማስ መሪ ግብጽ መግባቱን ቡድኑ አስታወቀ
በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ባለፈው ጥቅምት ወር ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሀንየህ ግብጽን ሲጎበኙ የአሁኑ ሁለተኛቸው ነው
የሀማስ መሪ ሀኒየህ ከግብጽ ባለስልጣናት በጋር በጋዛ እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ወቅታዊ ሁኔታ ለመመከር ካይሮ መግባቱን አስታውቋል
የሀማስ መሪ ግብጽ መግባቱን ቡድኑ አስታወቀ።
የሀማስ መሪ እስማኤል ሀኒየህ ከግብጽ ባለስልጣናት በጋር በጋዛ እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ወቅታዊ ሁኔታ ለመመከር በዛሬው እለት ካይሮ መግባቱን ቡድኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ኤኤፍ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው መቀመጫቸውን ኳታር ያደረጉት ሀንየህ ከግብጽ የደህንነት ኃላፊ ከሆኑት አባስ ካሜል ጋር ይነጋገራሉ።
እንደዘገባው ከሆነ ውይይቱ የእስራኤልን "ወረራ እና ጦርነት" በማስቆም እና እስረኞችን በማስለቀቅ እና በጋዛ ላይ የተጣለውን ከበባ በማስቀረት ዙሪያ የሚያተኩር ነው።
በግብጽ እና በአሜሪካ ድጋፍ፣ በኳታር ዋና አደራዳሪነት ባለፈው ወር በተካሄደው ለሳምንት በዘለቀው ተኩስ ጋብ የማድረግ ስምምነት፣ 80 የእስራኤል ታጋቾች ሲለቀቁ 240 ፍልስጤማውያን እስረኞች ደግሞ ተፈተዋል።
በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ባለፈው ጥቅምት ወር ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሀንየህ ግብጽን ሲጎበኙ የአሁኑ ሁለተኛቸው ነው።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንጃሚን ኒታንያሁ ታጋቾች የሚለቀቁበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሞሳድ ኃላፊን ወደ ሁለት ጊዜ ወደ አውሮፖ መላካቸውን በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
"በጉዳዩ ላይ የማላደርገው ጥረት አይኖርም፤ ሁሉንም ማስለቀቅ ኃላፊነታችን ነው"
ከታጋቾች ቤተሰቦች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ኔታንያሁ "ሁሉንም በህይወት ማስለቀቅ ትልቁ ስራችን ነው" ብለዋል።
የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ ባካሄዱበት ወቅት ነጭ ጨርቅ ሲያውለበልቡ ነበር የተባሉትን የእስራኤል ታጋቾች በስህተት መግደላቸውን ተከትሎ የታጋቾች ቤተሰቦች ተናደዋል፣ ተኩስ እንዲቆምም ጠይቀዋል።
በጋዛ እየተካሄ ባለው ጦርነት ከ19ሺ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
በጋዛ ያለው ሰብአዊ ቀውስ ለማስቆም በተመድ የጸጥታው ምክርቤት ቀርቦ የነበረው የተኩስ አቁም የውሳኔ ሀሳብ በአሜሪካ ተቃውሞ ምክንያት ሳይጸድቅ መቅረቱ ይታወሳል።