የእስራኤል ድብደባ በጋዛ አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት የመድረስ እድሉን እያጠበበ ነው - ኳታር
ዶሃ ሁለቱም ተፋላሚ ሃይሎች ተኩስ እንዲያቆሙ ማደራደሯን እንደምትቀጥል አስታውቃለች
የመንግስታቱ ድርጅት፣ ሩሲያ እና የተለያዩ የአረብና ሙስሊም ሀገራት የአሜሪካን ጣልቃገብነት እየተቃወሙ ነው
የእስራኤል የቦምብ ድብደባ በጋዛ አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት የመድረስ እድሉን እያጠበበው ይገኛል አሉ የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱልራህማን አልታኒ።
የዶሃ ፎረም ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱም ወገኖች የቀድሞው ፈቃደኝነታቸው አሁን ላይ እንደማይታይ ነው የተናገሩት።
እስራኤልና ሃማስ ለሰባት ቀናት የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ያደራደረችው ኳታር አሁንም ጥረቷን ስለመቀጠሏም አንስተዋል።
“ጦርነቱን ለማስቆም እና ታጋቾችን ለማስለቀቅ የምናደርገው ጥረት ቀጥሏል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እስራኤል እየወሰደችው ያለው እርምጃ መጠናከሩ የተኩስ አቁም ስምምነት የመድረስ እንቅስቃሴውን ክፉኛ እየፈተነው እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒይ ጉቴሬዝ በበኩላቸው በጸጥታው ምክርቤት ያለው “ጽንፍ የያዘ የጂኦስትራቴጂክ ክፍፍል” ለጋዛው ጦርነት መፍትሄ ለማበጀት የሚደረገውን ጥረት እያወከ ነው ብለዋል።
ለጦርነቱ ፈጣን ምላሽ መስጠት አለመቻሉም በመንግስታቱ ድርጅት ተአማኒነት ላይ ጥላውን ማሳረፉንም በማከል።
ዋና ጸሃፊው የመንግስታቱ ድርጅት ማቋቋሚያ ቻርተር አንቀጽ 99ን ተጠቅመው የጸጥታው ምክርቤት በጋዛ ጦርነት ዙሪያ አፋጣኝ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ያቀረቡት ጥያቄ በአሜሪካ ተቃውሞ ሳይሳካ መቅረቱን ፍራንስ 24 አስታውሷል።
በዶሃው ጉባኤ በቪዲዮ መልዕክት ያስተላለፉት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ፥ “ሞስኮ የጥቅምቱ 7ቱን የሃማስ ጥቃት ብታወግዝም እስራኤል ይህን እንደመነሻ በመውሰድ በሚሊየኖች ፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት መክፈቷን እንቃወማለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
የፍልስጤሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሀመድ ሽታየህም አሜሪካ እንደ እስራኤል ሁሉ በጋዛ እየተፈጸመ ለሚገኘው ፍጅት ተጠያቂ ናት ብለዋል።
የዮርዳኖስና ሌሎች የአረብና ሙስሊም ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም በዶሃው ምክክር እስራኤልና አሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠናን ወደ ትርምስ የሚከት እርምጃቸውን እንዲያቆሙ አሳስበዋል።
እስራኤል በበኩሏ የሚቀርቡ የተኩስ አቁም ጥያቄዎችን ወደጎን በመተው በሰሜንና ደቡብ ጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ መቀጠሏን ሬውተርስ ዘግቧል።
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው በእስራኤል የምድርና የአየር ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ18 ሺህ በላይ የደረሰ ሲሆን፥ ከ46 ሺህ በላይ ሰዎችም ቆሰለዋል።
እስራኤል በትናንትናው እለት ሃማስ እጁን እንዲሰጥ ጥሪ ያቀረበች ሲሆን፥ የፍልስጤሙ ቡድን በበኩሉ በእስራኤል የታሰሩ ፍልስጤማውያን ካልተለቀቁ አንድም ታጋች ከጋዛ በህይወት አይወጣም ብሏል።