ሃማስ በእስራኤል ንጹሃንን አልገደለም - የቡድኑ ምክትል የፖለቲካ መሪ
የአል ቃሳም ብርጌድ አዛዥ ሞሀመድ ኤል ዴይፍ እስራኤላውያን ንጹሃን እንዳይነኩ ማሳሰባቸውንም ነው ሙሳ አቡ ማርዙክ የተናገሩት
ሃማስ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ድብደባ ካላቆመች የታገቱ ሰዎችን እንደማይለቅም ገልጸዋል
የሃማስ የፖለቲካ ምክትል መሪው ሙሳ አቡ ማርዙክ ሃማስ በጥቅምት 7ቱ ጥቃት እስራኤላውያን ንጹሃንን መግደሉን አስተባበሉ።
ምክትል መሪው ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሃማስ በእስራኤል ወታደሮችን ብቻ ኢላማ ያደረገ ጥቃት መፈጸሙን ተናግረዋል።
እስራኤል ሃማስ ከአንድ ወር በፊት በፈጸመው ጥቃት ከ1 ሺህ 400 በላይ ዜጎቿ መገደላቸውንና አብዛኞቹም ንጹሃንን መሆናቸውን መግለጿ የሚታወስ ነው።
ቡድኑ መሳሪያ ያልታጠቁ ህጻናት እና ወጣቶችን ሲገድል የሚያሳዩ ምስሎችም ወጥተዋል።
የሃማስ የፖለቲካ ምክትል መሪው ሙሳ አቡ ማርዙክ ግን ሃማስ እስራኤላውያን ንጹሃንን አልገደለም ብለው ተከራክረዋል።
የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ አል ቃሳም ብርጌድ አዛዥ ሞሀመድ ኤል ዴይፍ ለቡድኑ ታጣቂዎች እስራኤላውያን ህጻናትን፣ እናቶችን እና አዛውንቶችን እንዳይገድሉ ማሳሰባቸውንም ይጠቅሳሉ።
የሃማስ የፖለቲካ ክንፍ ስለ ጥቅምት 7ቱ ጥቃት ዝግጅት ያውቅ እንደነበር ተጠይቀውም ወታደራዊው ክንፍ ከፖለቲካ መሪዎች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መነጋገር አይጠበቅባቸውም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በኳታር የሚገኘው የሃማስ የፖለቲካ ክንፍ ራሱን ከወታደራዊው ክንፍ ለመለያየት ጥረት ሲያደርግ ቢታይም ብሪታንያን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ሁለቱንም በሽብርተኝነት ፈርጀዋል።
ሙሳ አቡ ማርዙክም በአሜሪካ በአለማቀፍ ሽብርተኝነት የተፈረጁ ሲሆን፥ ብሪታንያም ሃብታቸው እንዳይንቀሳቀስ ማገዷ የሚታወስ ነው።
የሃማስ ምክትል የፖለቲካ መሪው በቡድኑ ስለታገቱ ሰዎች ተጠይቀውም እስራኤል በጋዛ ድብደባዋን እስካላቆመች ድረስ አንድም ታጋች አይለቀቅም ሲሉ ተደምጠዋል።
“እስራኤል ጦርነቱን ካቆመች ታጋቾቹን ለቀይ መስቀል እናስረክባለን” የሚል ምላሽም ሰጥተዋል።
ሙሳ አቡ ማርዙክ በቅርቡ ወደ ሞስኮ በማቅናት ታጋቾቹ ስለሚለቀቁበት ሁኔታ መምከራቸው የሚታወስ ነው።
32ኛ ቀኑን በያዘው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ህይወታቸው የተቀጠፈ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ10 ሺህ በላይ መድረሱን የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።