የሀማስ መሪ ከእስራኤል ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ተቃርበናል አለ
ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረቡን የገለጸው ቡድኑ ተጨማሪ ዝርዝር አልሰጠም
የአይሲአርሲ ፕሬዝደንት ሚርጃና ስፖልጃሪክ ከሀየንያህ ጋር በኳታር በሰብአዊ ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገራቸውን አይሲአርሲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል
ሀማስ ከእስራኤል ጋር "የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረቡን" ገለጸ
እስራኤል በጋዛ ላይ እየወሰደች ያለው ጠንካራ ጥቃት በቀጠለበት እና ሮኬቶች ወደ እስራኤል እየተወነጨፉ ባለበት ወቅት፣ የሀማስ መሪ ከእስራኤል ጋር "የኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ተቃርበናል" ብሏል።
የሀማስ ባለስልጣናት ከእስራኤል ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ መቃረባቸውን እና ቡድኑ ለኳታር አደራዳሪዎች መልስ መስጠቱን የቡድኑ መሪ እስማኤል ሃኒየህ ለሮይተርስ ገልጿል።
ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረቡን የገለጸው ቡድኑ ተጨማሪ ዝርዝር አለመስጠቱን ዘገባው ጠቅሷል።
ነገርግን ቀደም ሲል በወጡ መረጃዎች ሀማስ እና እስራኤል ታጋቾችን በመልቀቅ፣ እርዳታ በማድረስ እና ተኩስ አቁሙ ለስንት ቀይ ይሁን በሚሉት ነጥቦች ላይ በኳታር አደራዳሪነት ተነጋግረዋል።
ሃማስ ባለፈው ጥቅምት ወር ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለትን የእስራኤል ድንበር ጥሶ በመግባት 1200 ሰዎችን ሲገድል 240 የሚሆኑትን ደግሞ አግቶ መውሰዱ የሚታወስ ነው።
የአለምአቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር(አይሲአርሲ) ፕሬዝደንት ሚርጃና ስፖልጃሪክ ከሀየንያህ ጋር በኳታር መገናኘታቸውን እና የሰብአዊ ጉዳዮችን በማሻሻል ዙሪያ መነጋገራቸውን አይሲአርሲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ስፖልጃሪክ ከኳታር ባለስልጣናት ጋርም በተናጠል መወያየታቸውን ተናግረዋል።
ታጋቾች እንዲለቀቁ አላማ ያደረገው ድርድር አካል አለመሆኑን የገለጸው አይሲአርሲ ነገርግን እንደገለልኛ አካል ሁለቱ አካላት ታጋቾችን ለመልቀቅ የሚስማሙ ከሆነ ለማመቻቸት ዝግጁ ነኝ ብሏል።
በአሜሪካ የእስራኤል አምባሳደር ሚካኤል ሄርዞግ ሀማስ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ በርካታ ታጋቾችን ይለቃል ብለው ተስፋ እንደማያደርጉ ተናግረዋል።
አምባሳደሩ ይህን ያሉት የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር በሀማስ እና በእስራኤል መካከል እየተደረገ ያለው ድርድር "ጥቂት ነገር" ብቻ ይቀረዋል ማለታቸውን ተከትሎ ነው።
ሼህ መሀመድ ቢን አብዱልራህማን አል ታኒ በዋናነት "የተግባር እና የሎጂስቲክ" ጉዳዮች እንደቀሩት ነበር የገለጹት።
ሀማስን ከምደረ ገጹ ለማጥፋት የወሰነችው እስራኤል ተኩስ አቁምን እንደማትቀበለው መግለጿ ይታወሳል።