የሲንዋር መገደል የፍልስጤማውያንን የትግል መንፈስ ይበልጥ ያጠናክረዋል - ኢራን
የሊባኖሱ ሄዝቦላህም የሃማሱን መሪ ግድያ ተከትሎ በእስራኤል ላይ የምፈጽመውን ጥቃት ወደ አዲስ ምዕራፍ እሸጋገራለሁ ብሏል
ምዕራባውያን የሲንዋር መገደል የጋዛው ጦርነት እንዲቋጭ ያደርጋል ቢሉም ኔታንያሁ ግን ታጋቾች ሳይለቀቁ ጦርነቱ አይጠናቀቅም ብለዋል
ኢራን በሃማስ መሪ ግድያ የፍልስጤማውያን የትግል መንፈስ ይበልጥ ይጠናከራል እንጂ አይዳከምም አለች።
እስራኤል በትናንትናው እለት በሀምሌ ወር በቴህራን የተገደሉትን የሃማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ የተኩት ያህያ ሲንዋር በጋዛ መገደላቸውን ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።
በመንግስታቱ ድርጅት የኢራን ተልዕኮ የሲንዋር መገደል ቴህራን ለፍልስጤማውያን የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቋርጥ እንደማያደርጋት የሚጠቁም መግለጫ አውጥቷል።
“የሲንዋር ግድያ የትግል መንፈስን ይበልጥ ያጠነክራል” በማለትም የሃማሱ መሪ መገደል የፍልስጤማውያንን የረጅም አመታት የነጻነት ትግል ወደኋላ እንደማያስቀረው አብራርቷል።
የሊባኖሱ ሄዝቦላህም ግድያውን ተከትሎ በእስራኤል ላይ “አዲስ እና ከባድ ጥቅት እክፈታለሁ” ሲል ዝቷል።
በእስራኤል ላይ በየእለቱ የሮኬት ጥቃቶችን እየፈጸመ የሚገኘው ሄዝቦላህ ምን አይነት እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ፍንጭ አልሰጠም።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በመደወል የደስታ መልዕክታቸውን ሲገልጹ፥ የሲንዋር መገደል የጋዛው ጦርነት እንዲቆምና እስራኤላውያን ታጋቾች እንዲለቀቁ በር ይከፍታል ብለዋል።
ያህያ ሲንዋር በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይደረሰ “ዋነኛው እንቅፋት ነበር” ያሉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ማቲው ሚለር፥ ዋሽንግተን የተኩስ አቁም ንግግር በፍጥነት እንዲጀመር ትፈልጋለች ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የቴል አቪቭ አጋር ዋሽግተን የሲንዋር ግድያ የጋዛውን ጦርነት ለመቋጨት ትልቅ ብስራት ነው ብትልም የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦርነቱ ታጋቾች እስከሚለቀቁ ድረስ ይቀጥላል ብለዋል።
እስራኤላውያን የታጋቾቹ ቤተሰቦችም የጥቅምት 7ቱን ጥቃት አቀናብሯል የተባለው ያህያ ሲንዋር መገደል ትልቅ ድል መሆኑን ጠቅሰው የኔታንያሁ አስተዳደር ከአንድ አመት በላይ በጋዛ ለሚሰቃዩ ታጋቾች እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል።
ምዕራባውያን ሀገራት የያህያ ሲንዋር ግድያ የጋዛውን ጦርነት ያስቆማል በሚል ለእስራኤል የደስታ መግለጫቸውን እየሰደዱ ነው። ይሁን እንጂ የሃማስም ሆነ የሄዝቦላህ መሪዎች መገደል በጋዛም ሆነ በሊባኖስ ጦርነትን በፍጥነት ሲገታ አልታየም ይላሉ ተንታኞች።
ሬውተርስ በካን ዩኒስ ያነጋገረው ፍልስጤማዊ ተፈናቃይ ታቤት አሙርም “ትግላችን የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ የሚቆም አይደለም፤ የሲንዋር መገደልም ትግሉን አያስቆመውም ወይም ነጭ ባንዲራ አውጥተን እጅ እንድንሰጥ አያደርገንም” ብሏል።