በጋዛ ተኩስ አቁም ዙሪያ በአሜሪካ ፣ እስራኤል እና ሀማስን ያላስማማው ጉዳይ ምንድን ነው?
አሜሪካ ሀማስን “ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉ” ጥያቄዎችን በማቅረብ ከሳለች

እስራኤል በሀማስ ላይ ጫና ለማበርታት የኤሌክትሪክ አገለግሎትና የእርዳታ ስርጭት እንዲቆም አድርጋለች
የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማራዘም በአሜሪካ ፣ እስራኤል እና ሀማስ መካከል በኳታር የተደረገው ውይይት ካለ ስምምነት መጠናቀቁን ተነግሯል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፈችው አሜሪካ ሀማስ “ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉ” ጥያቄዎችን በማቅረብ ከሳለች፡፡
የመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት በመጋቢት 1 ከተጠናቀቀ በኋላ ተደራዳሪዎች ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ለመወሰን በድርድር ላይ ናቸው፡፡
አሜሪካ የመጀመሪያው ምዕራፍ እስከ ሚያዚያ አጋማሽ ድረስ እንዲራዘም እና በዚህ ጊዜ ውስጥም የታጋች እና የእስረኛ ልውውጡ እንዲቀጥል ሀሳብ አቅርባለች፡፡
የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ባቀረቡት በዚህ ሀሳብ እስራኤል የተስማማች ቢሆንም ሀማስ ሀሳቡን አንደማይቀበለው ገልጿል፡፡
ሀማስ የእስራኤል ጦር ከጋዛ እንዲወጣ የሚጠይቀው እና በዘላቂ ጦርነት ማቆም ላይ የሚመክረው ሁለተኛው ዙር የተኩስ አቁም ምዕራፍ አሁኑኑ ተግባራዊ መደረግ እንዲጀምር ጠይቋል፡፡
ከዚህ ባለፈ በመጀመሪያው ዙር ምዕራፍ ተጋቾች እና እስረኞችን እየተለዋወጡ መቀጠል ለጦርነቱ በዘላቂነት መቆም ማስተማመኛ ሊሆን እንደማይችል ሀሳቡን መግለጹን በድርድሩ የተሳተፉ የፍልስጤም ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
እስራኤል እና ሃማስ ከ15 ወራት ጦርነት በኋላ በጥር ወር ሶስት እርከኖችን ያካተተ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡
ለአንድ ወር በቆየው የመጀመሪያ ምዕራፍ ሃማስ 25 በህይወት ያሉ የእስራኤል ታጋቾችን፣ ስምንት አስክሬኖችን እና አምስት በህይወት ያሉ የታይላንድ ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል 1800 የሚጠጉ ፍልስጤማውያን እስረኞችን በምትኩ ፈታለች፡፡
ነገር ግን ሁለቱ ወገኖች በመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት አፈጻጸም ፣ በቀጣይ በሚለቀቁ ታጋቾች ቁጥር እና የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ መውጣት በሚጀምሩበት ሂደት ዙሪያ መስማማት ተስኗቸዋል፡፡
ይህን ተከትሎም እስራኤል በሃማስ ላይ ጫና ለመፍጠር ያለመ ነው ባለችው እርምጃ የምግብ እና ነዳጅ አቅርቦትን ጨምሮ ለጋዛ የምትሰጠውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት አቁማለች።
በአሁኑ ወቅት በሃማስ እጅ 24 የሚደርሱ ታጋቾች እና የ35 ሰዎች አስክሬን እንደሚገኝ ይታመናል።
የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ “ሀማስ በተቀመጠለት ቀነ ገድብ ለስምምነት የማይቀርብ ከሆነ ጦርነቱ ድጋሚ ላለመጀመሩ ዋስትና የለውም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እስራኤል ካለ ስምመነት በተበተነው የኳታሩ ጉባኤ ዙሪያ ይፋዊ መግለጫን ባታወጣም የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ከእስራኤላውን ተደራዳሪዎች ማብራርያ ከተደረገለት በኋላ ስለቀጣይ እርምጃው መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡