እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት ሶስት ጋዜጠኞችን ጨምሮ 11 ፍልስጤማውያን ተገደሉ
ሃማስ ከጥር ወሩ የተኩስ አቁም ስምምነት ወዲህ በእስራኤል የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 150 መድረሱን አስታውቋል

የእስራኤል ጦር በበኩሉ ጥቃቱን የፈጸመው በንጹሃን ላይ ሳይሆን በሽብርተኞች ላይ መሆኑን ገልጿል
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት በጥቂቱ የ11 ሰዎች ህይወት ማለፉን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
በሰሜናዊ ጋዛ ቤት ላሂያ ከተማ በተሽከርካሪ ላይ የተፈጸመው የአየር ጥቃት ሶስት ጋዜጠኞችን ጨምሮ የዘጠኝ ፍልስጤማውያንን ህይወት ቀጥፎ በርካቶችን ማቁሰሉ ተነግሯል።
ተሽከርካሪው ውስጥ "አል ካሂር" የተሰኘ የእርዳታ ፋውንዴሽን በቤት ላሂያ ከተማ የሚያደርገውን ድጋፍ ሽፋን የሚሰጡ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ሰራተኞች እንደነበሩ ነው ሚኒስቴሩ የጠቀሰው።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ ተሽከርካሪው ውስጥ የነበሩ "ሽብርተኞች" ድሮን ማንቀሳቀሳቸውን በአካባቢው ለሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች የደህንነት ስጋት በመደቀኑ ጥቃቱ መፈጸሙን ገልጿል።
ስድስቱ ህይወታቸው ያለፈ ፍልስጤማውያን የሃማስ ኛ ኢስላሚክ ጂሃድ አባላት መሆናቸውንና የተወሰኑት ታጣቂዎች "በጋዜጠኝነት ሽፋን የሽብር ተግባር የሚፈጽሙ" መሆናቸውንም ነው ያስታወቀው።
የአየር ጥቃቱ በጥር 19 2025 መተግበር የጀመረው የጋዛ ተኩስ አቁም አደጋ ላይ መውደቁን ያሳያል ተብሏል።
የፍልስጤም የጤና ባለስልጣናት እስራኤል በተኩስ አቁም ስምምነቱ ወቅትም ጥቃቷን እንዳላቆመች ይናገራሉ።
የጋዛ የመንግስት የሚዲያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሳላማ ማሩፍ የእስራኤል ጦር ለትናንቱ የአየር ጥቃት ያቀረበውን ምክንያት ውድቅ አድርገዋል።
"በድንኳን ውስጥ ለተጠለሉ ሰዎች ድጋፍ ለማድረስ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቡድን አባላት ሁሉም ንጹሃን ናቸው፤ በተከለከለ ስፍራ አልነበሩም፤ (ለእስራኤል ወታደሮች) ምንም አይነት ስጋት የሚደቅን ተግባር አልፈጸሙም" ብለዋል።
እስራኤል በማዕከላዊ ጋዛ ጁሀር ኤልዴክ ከተማ በፈጸመችው ጥቃትም ሁለት ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተገልጿል። የእስራኤል ጦር ግን ስለጥቃቱ የማውቀው ነገር የለም ማለቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
ሃማስ በጋዛ ተኩስ ለማቆም ስምምነት ከተደረሰ ወዲህ እስራኤል በፈጸመቻቸው ጥቃቶች የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 150 ደርሷል ሲል ወቅሷል።
አደራዳሪዎችም እስራኤል በምዕራፍ ወደተከፋፈለው የተኩስ አቁም ድርድር እንድትመለስ ጫና እንዲያደርጉባት ነው የጠየቀው።
የእስራኤል ጦር ከሃማስ ለቀረበበት ወቀሳ ምላሽ ሲሰጥ የእስራኤል ወታደሮች በሚገኙባቸው ስፍራዎች አካባቢ ቦምቦችን የመቅበርና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት እርምጃ መውሰዱን ገልጿል።
የእስራኤልና ሃማስ የመጀመሪያ ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ከሁለት ሳምንት በፊት መጠናቀቁን ተከትሎ በግብጽ፣ ኳታር እና አሜሪካ አደራዳሪነት ሲካሄዱ የነበሩ ንግግሮች እስካሁን ውጤት አላስገኙም።
የሃማስ መሪ ካሊል አል ሃያ በሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ዙሪያ ለመምከር ካይሮ የገቡ ሲሆን፥ ከስምምነት ላይ ካልተደረሰ እስራኤል በጋዛ ዳግም ጦርነት ልትጀምር እንደምትችል ተሰግቷል።