አሜሪካ የጥቅምት 7ቱን ጥቃት አቀነባብረዋል ባለቻቸው የሃማስ መሪዎች ላይ ክስ መሰረተች
የወንጀል ክስ ከተመሰረተባቸው ውስጥ የሃማስ መሪ ያህያ ሲንዋር እና በኳታርና ሊባኖስ የሚገኙ የቡድኑ አመራሮች ይገኙበታል
በጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት ከተገደሉት 1 ሺህ 200 ገደማ ሰዎች ከ40 በላዩ የአሜሪካ ዜጋ ነበሩ ተብሏል
አሜሪካ የጥቅምት 7ቱን ጥቃት አቀነባብረዋል ባለቻቸው የሃማስ መሪዎች ላይ የወንጀል ክስ መስርታለች።
የሀገሪቱ ፍትህ ሚኒስቴር በትናንትናው እለት ከ40 በላይ አሜሪካውያን ህይወት የተቀጠፈበትን ጥቃት መርተዋል፤ አስተባብረዋል ባላቸው ስድስት የሃማስ አመራሮች ላይ ክስ መመስረቱን ገልጿል።
“ተከሳሾቹ ከኢራን እና ከሊባኖሱ ሄዝቦላህ የጦር መሳሪያ እና የፖለቲካ ድጋፍ በማሰባሰብ የሃማስን እስራኤልን የማጥፋት አላማ ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል፤ አላማቸውን ለማሳካትም ንጹሃንን ገድለዋል” ብለዋል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሜሪክ ጋርላንድ።
ክስ ከተመሰረተባቸው ስድስት የሃማስ አመራሮች ውስጥ ሶስቱ ህይወታቸው አልፏል።
የቀድሞው የሃማስ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ፣ የቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ መሪ ሞሀመድ ዴይፍ እና ምክትል ወታደራዊ አዛዡ ማርዋን ኢሳ በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል።
በህይወት ያሉት ተከሳሾች ሃኒየህን የተኩትን በጋዛ እንደሚገኙ የሚታመነው ያህያ ሲንዋር፣ የሃማስን የዲያስፖራ ቢሮ የሚመሩትና በዶሃ የሚገኙት ካሌድ መሻል እንዲሁም በሊባኖስ የሚኖሩት ከፍተኛ የቡድኑ አመራር አሊ ባራካ ናቸው።
አሜሪካ በስድስቱም የሃማስ አመራሮች ላይ የወንጀል ክስ ለመመስረት ያሰበችው በየካቲት ወር እንደነበር የጠቀሰው ሬውተርስ፥ ኢስማኤል ሃኒየህ በቁጥጥር ስር ይውላል በሚል ተስፋ ክሱ መዘግየቱን ዘግቧል።
የሃኒየህ ግድያ ከተሰማ በኋላም የአሜሪካ ፍትህ ሚኒስቴር ክሱ እንዲመሰረት መወሰኑ ነው የተጠቆመው።
ሃማስን በሽብርተኛ ድርጅትነት የመዘገበችው አሜሪካ ከ40 በላይ ዜጎቿን ጨምሮ 1 ሺህ 200 ገደማ ሰዎች የተገደሉበትንና በመቶዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን የታገቱበትን የጥቅምት 7 ጥቃት “ጥቁር ቀን” ነው ብላለች።
ይህን ጥቃት መርተዋል ባለቻቸው የቡድኑ መሪዎች ላይም ተደጋጋሚ ማዕቀቦችን ስትጥል ቆይታ ክስ መስርታለች።
ይሁን እንጂ ለ11 ወራት ባላባራው የጋዛ ድብደባ ከ40 ሺህ 800 በላይ ፍልስጤማውያን እንዲገደሉ፤ ሚሊየኖች እንዲፈናቀሉ ትዕዛዝ የሚሰጡ የእስራኤል ባለስልጣናትን በዝምታ በማለፍ ድጋፏን አሳይታለች።