ኢስማኤል ሃኒየህ - ከስደተኞች ጣቢያ እስከ ሃማስ ፖለቲካ ቢሮ መሪነት
በአዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ለመታደም ባመሩበት የተገደሉት ኢስማኤል ሃኒየህ ስርአተ ቀብር በዶሃ ተፈፅሟል
በእስራኤል ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ሃኒየህ ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ትኩረት ሰጥተው ለፍልስጤም ነፃነት ሲታገሉ ቆይተዋል
በፈረንጆቹ 1963 በአል ሻቲ የስደተኞች ጣቢያ የተወለዱት ሃኒየህ በ1989 በተካሄደው የመጀመሪያው የፍልስጤማውያን “ኢንቲፋዳ” (አመፅ) ከተሳተፉ ጀምሮ በእስራኤል በአይነ ቁራኝ የሚጠበቁ ሆነዋል።
ቴል አቪቭ ከእስር ስትለቀቃቸውም ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ በማስወጣት ከትግሉ እንዲርቁ ለማድረግ ብትሞክርም ከሶስት አስርት አመታት በላይ የግድያ ሙከራዎችን እያመለጡ ለፍልስጤም ነፃነት ሲታገሉ ቆይተዋል።
በፈረንጆቹ 2006 ሃማስ በፍልስጤም ምርጫ ሲያሸንፍ የፋታህ መሪውና የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ሃኒየህ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ አጭተዋቸው ነበር።
ይሁን እንጂ ሃማስ በምዕራባውያኑ ስላልተወደደ እስራኤል ጭምር ትደግፈዋለች የሚባለው ፋታህ የሃኒየህን እጩነት ሰርዞ ሁለቱ የፍልስጤም ሀይሎች ጦር መማዘዛቸው ይታወሳል።
ሀኒየህ በ2017 የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ ሃላፊ ሆነው ከተሾሙ በኋላ መቀመጫቸውን ኳታርና ቱርክ በማድረግ ፋታህን ጨምሮ ከተለያዩ የፍልስጤም ሃይሎች ጋር በሚደረጉ ድርድሮች ላይ ተሳትፈዋል።
እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረች ወዲህም የፍልስጤማውያን ሰቆቃ እንዲቆም በኳታርና ግብፅ ሸምጋይነት በተደረጉ ድርድሮች ሲሳተፉ ቆይተዋል።
ከቤጂንግ እስከ ሞስኮ፤ ከቤሩት እስከ አንካራ፤ ከቴህራን እስከ ካይሮ በመመላለስ ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ያሳዩት ጥረትም አጥብቃ በምትፈልጋቸው እስራኤል የተወደደላቸው አይመስልም።
ሶስት ልጆቻቸው እና አራት የልጅ ልጆቻቸው በእስራኤል ጥቃት ሲገደሉባቸው "የልጆቼ ደም ከሁሉም ፍልስጤማውያን የተለየ አይደለም፤ ግድያው ትግሉን አይቆመውም" ብለው የተናገሩት ኢስማኤል ሀኒየህ፥ ሀምሌ 24 2016 የልጆቻቸው እጣ ደርሷቸዋል።