ካይሮ 20 የሚጠጉ ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ ድንበሯን ለመክፈት መስማማቷ ተነግሯል
ግብጽ ለፍልስጤማውያን እርዳታ እንዲደርስ የጋዛ ሰርጥ ድንበሯን ለመክፈት መስማማቷ ተነግሯል።
በጋዛ መውጫና መግቢያ ያጡ 2.3 ሚሊዮን ሰዎች ሰብዓዊ ቀውሱ እየተባባሰ ሲሆን፤ ጸረ-እስራኤል ተቃውሞዎችም በመካከለኛው ምስራቅ ተቀስቅሰዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከስምንት ሰዓት ያነሰ የእስራኤል ጉብኝት በኋላ ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤል ሲሲ ጋር ለጋዛ እርዳታ ለማቅረብ በስልክ ተወያይተዋል።
- ግብጽ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ወደ ሲናይ ማፈናቀል ከእስራኤል ጋር ጦር ያማዝዘኛል አለች
- በእስራኤል የሚገኙት ባይደን የጋዛው ፍንዳታ የተፈጸመው በታጣቂዎች ነው አሉ
ባይደን ፕሬዝዳንት ሲሲ ወደ 20 የሚጠጉ ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከግብጽ ወደ ጋዛ እንዲገቡ የራፋ ድንበርን ለመክፈት መስማማታቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ባይደን የድንበሩን መክፈቻ የጊዜ ሰሌዳ ባይናገሩም፤ የሀገሪቱ የብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ ጆን ከርቢ የመንገድ ጥገና ከተደረገ በኋላ በሚቀጥሉት ቀናት እርዳታው እንደሚደርስ ገልጸዋል።
የእስራኤል-ሀማስ ግጭት ከሁለቱ ሀገራት አልፎ ሊሰራጭ ይችላል በሚል ስጋት ባይደን የአረብ መሪዎችን ለማግኘት አቅደው ነበር ተብሏል።
ነገር ግን ከጋዛ ሆስፒታሉ ፍንዳታ በኋላ ከግብጽ እና ከፍልስጤም አስተዳደር ጋር ሊደረግ የታቀደውን ስብሰባ ዮርዳኖስ ሰርዛለች።
ማክሰኞ ምሽት በጋዛ አል አህሊ አል አራቢ ሆስፒታል ላይ የደረሰው ፍንዳታ ውጥረቱን አባብሷል።
በፍንዳታው የፍልስጤም ባለስልጣናት 471 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቀው፤ የእስራኤል የአየር ጥቃትን ወቅሰዋል።
እስራኤል እና አሜሪካ ፍንዳታው በእስላማዊ ታጣቂዎች የደረሰ የከሸፈ ሮኬት ነው ብለዋል።