ሀማስ በአሜሪካ የአደራዳሪነት ሚና ላይ እምነት ማጣቱን ገለጸ
ቡድኑ በተለያዩ ወቅቶች የተደረጉ ድርድሮች ወደ ትግበራ ከመግባት ይልቅ አዳዲስ ሀሳቦች የሚቀርቡባቸው ሆነዋል ብሏል
ሩስያ ፣ ቱርክ እና ተመድ በአደራዳሪነት እንዲካተቱ ሀማስ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል
ሀማስ በአሜሪካ የማደራደር አቅም ላይ እምነት እንዳጣ አስታወቀ፡፡
የቡድኑ ከፍተኛ ሀላፊ የሆኑት ኦሳማ ሀምዳን ከአሶሼትድ ፕረስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ እስካዛሬ በነበሩ የድርድር መድረኮች ላይ የተስማማንባቸውን ሀሳቦች ከመፈጸም ይልቅ አዳዲስ ሀሳቦች እየቀረቡ የድርድሩን ሂደት አረዝመውታል ብለዋል፡፡
በዛሬው እለት በኳታር ወይም ግብጽ እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት በነበረው ድርድር ላይ እንደማይሳተፍ ያስታወቀው ሀማስ ቀደም ሲል አሜሪካ ባቀረበችው እና የጸጥታው ምክር ቤት ድጋፍ በሰጠው የስምምነት ሰነድ ትግበራ ላይ ካልሆነ ከእስራኤል ጋር አልነጋገርም ብሏል፡፡
የሃማስ ከፍተኛ ሀላፊው እስማኤል ሀምዳን “ለአደራዳሪዎቹ ከዚህ በኋለ የትግበራውን ሂደት እና ለመተግበር የሚወስደውን የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ ላይ መወያየት ስትፈልጉ ጥሩን ብለናቸዋል” ነው ያሉት፡፡
ሀላፊው እስካሁን በተደረጉ ድርድሮች እስራኤል የምትልካቸው ልኡካኖች በየጊዜው የሚቀያየሩ ከመሆናቸው ባለፈ በውሳኔ ሀሳቦች ላይ ድምጽ መስጠት የማይችሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
አሜሪካም ምንም እንኳን ድርድሩን በማመቻቸት እና የስምምነት ሀሳቦችን በማቅረብ ዋና ተዋናይ ትሁን እንጂ በእስራኤል አስተዳደር ላይ ተገቢውን ተጽእኖ ማሳደር አልቻለችም ሲሉ ወቀሰዋል፡፡
ሀማስ እና እስራኤል በመካከለቸው የሚደረገውን ድርድር በማደናቀፍ እርስ በእርስ ይካሰሳሉ፡፡
የሀማስ ከፍተኛ ሀላፊው ኦሳማ ከአሶሼትድ ፕረስ ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ ባለፉት የድርድር መድረኮች ላይ የተወያዩባቸውን እና ያልተስማሙባቸውን የድርድር ሰነዶች ለማስረጃነት በማቅረብ ድርድሩ እንዳይሳካ ዋነኛ እንቅፋት ራሷ እስራኤል ናት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሃላፊው ባቀረቡት ሰነድ የድርድር ሂደቱ እንዲሳካ እና በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግ አሁን ካሉ አደራዳሪዎች በተጨማሪ ሀማስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፣ ሩስያ እና ቱርክ በድርድሩ ውስጥ እንዲሳተፉ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ መደረጉን ያመላክታል፡፡
እስራኤል በበኩሏ ሀማስ ለውይይት በቀረበው የድርድር ሰነድ ላይ 29 ነጥቦች እንዲቀየሩ በመጠየቅ ሂደቱ እንዲጓተት አድርጓል በሚል ትከሳለች፡፡
ኦሳማ ሀምዳን ለዚህ በሰጡት ምላሽ ሀማስ አሜሪካ ባቀረበችው የድርድር ሰነድ ነጥቦች ላይ ከ80 በመቶ በላይ መስማማቱን ተናግረዋል፡፡
ቡድኑ ለድርድር ፈቃደኛ መሆኑን በቅድሚያ እንዳስታወቀ በማስታወስም አሜሪካ እስካሁን እስራኤል የስምምነት ሰነዱን እንድትቀበል ማሳመን አልቻለችም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡