ኔታንያሁ የመከላከያ ሚኒስትራቸውን “ጸረ እስራኤላዊ ትርክት” ተጭኗቸዋል ሲሉ ወረፉ
ሚኒስትሩ ከሰሞኑ የኔታንያሁ አስተዳደር በሃማስ ላይ “ፍፁም የተሟላ ድል” አገኛለሁ ማለቱ የማይጨበጥ ነው ሲሉ መቃወማቸው ተገልጿል
ዮቭ ጋላንት በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የሚያቀርቡት ጥያቄ ከኔታንያሁ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ ከቷቸዋል ተብሏል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የመከላከያ ሚኒስትሩን ዮቭ ጋላንት “ጸረ እስራኤላዊ ትርክት” ተጭኗቸዋል ሲሉ ወረፉ።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት ከህግ አውጪዎች ጋር በዝግ በተካሄደ ምክክር የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁን የጋዛ ጦርነት ግብ ማጣጣላቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ጋላንት በጋዛ “ፍጹም የተሟላ ድል” ይገኛል በሚል በኔታንያሁ የተያዘው እቅድ “የማይጨበጥ” እና ስኬታማ ሊሆን የማይችል ነው ማለታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን አስቆጥቷል።
የኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫም የመከላከያ ሚኒስትሩ አስተያየት በጋዛ የሚገኙ ታጋቾችን ለማስለቀቅ የሚደረገውን ጥረት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብሏል።
ጋላንት “ጸረ እስራኤላዊ ትርክት” እየተጋባባቸው መሆኑን በመጥቀስም እስራኤል በጋዛ ለጀመረችው ጦርነት ሁለት ግቦች ተፈጻሚነት ስራቸውን በአግባቡ መቀጠል እንዳለባቸው አሳስቧል።
ሁለቱ መሰረታዊ ግቦችም ሀማስን ዳግም እንዳያንሰራራ አድርጎ መደምሰስና ከ10 ወራት በላይ በጋዛ ታግተው የሚገኙ እስራኤላውያንን ማስለቀቅ መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት አመላክቷል።
ኔታንያሁ እና ጋላንት ቃላት ሲወራወሩ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ሲጠይቁ ከኔታንያሁና ቀኝ ዘመም አጣማሪዎቻቸው ትችት እንደደረሰባቸው ሲኤንኤን አስታውሷል።
ኔታንያሁ የጥምር መንግስታቸውን ለማስቀጠል ሲሉ ተኩስ ከማቆም ይልቅ የጦርነቱን አድማስ ወደማስፋት ማዘንበላቸውም ከመከላከያ ሚኒስትሩ ጋር መቃቃር ውስጥ ሲከታቸው ቆይቷል ተብሏል።
ጋላንት በሊባኖስ ከወራት በፊት ጥቃት ለማድረስ ኔታንያሁ አልፈቀዱልኝም ሲሉ፥ ኔታንያሁ ደግሞ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳይደረስ እንቅፋት ሆኗል ያሉትን የሃማስ መሪ ያህያ ሲንዋር አድኖ መግደል የተሳነው ጋላንት ነው በማለት ይወቅሳሉ።
የእስራኤላውያን ታጋቾች ቤተሰቦች ደግሞ ኔታንያሁ በታጋቾች ህይወት ላይ "እየቆመረ" ነው በሚል ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግቧል።
እስራኤልና ሃማስን ሲያደራድሩ የቆዩት አሜሪካ፣ ግብፅ እና ኳታር ተፋላሚ ሀይሎቹ ዳግም ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጠይቀዋል።
ቀጣዩ የተኩስ አቁም ድርድር ከነገ በስቲያ ሃሙስ በካይሮ እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል።