ሃማስ በነገው እለት የሚለቀቁ ታጋቾችን ስም ይፋ አደረገ
አራተኛው ዙር የታጋቾችና እስረኞች ልውውጥ ሲደረግ እስራኤል 90 ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንደምትለቅ ተገልጿል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/1/31/273-180043-20250131-israeli-hostages-release-010225_700x400.jpg)
እስራኤል በትናንትናው እለት በካን ዩኒስ ታጋቾች ሲለቀቁ የተፈጠረው ትርምስ እንዳይደገም አሳስባለች
የፍልስጤሙ ሃማስ በነገው እለት ከጋዛ የሚለቃቸውን ታጋቾች ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ አልቃሳም ብርጌድ ቃልአቀባይ አቡ አቤይዳ በቴሌግራም ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ የሚለቀቁት ታጋቾች ኦፈር ካልዴሮን፣ ያርደን ቢባስ እና የአሜሪካ እና እስራኤል ጥምር ዜግነት ያላቸው ኬት ሲገል ናቸው ብለዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚለቀቁት ታጋቾች ስም ዝርዝር እንደደረሰው አረጋግጧል።
ሃማስ ሶስት ታጋቾችን ነገ ሲለቅ እስራኤል 90 ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንደምትፈታ ተገልጿል።
ከአራት የእስራኤል እስርቤቶች ከሚፈቱት ፍልስጤማውያን ውስጥ ዘጠኙ የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው መሆናቸውን የፍልስጤም የታራሚዎች ሚዲያ ቢሮ አስታውቋል።
ቴል አቪቭ ግን በነገው እለት ምን ያህል እስረኞች እንደሚለቀቁ ማረጋገጫ አልሰጠችም ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
እስራኤልና ሃማስ ተኩስ ለማቆም ከተስማሙበት እለት (ጥር 19 2025) ጀምሮ በሶስት ዙሮች 15 ታጋቾች ተለቀዋል።
እስራኤል ደግሞ 400 የእድሜ ልክ እና የረጅም አመታት እስር የተፈረደባቸውን ፍልስጤማውያን እስረኞች ፈታለች።
በነገው እለት የሚካሄደው አራተኛው ዙር የእስረኞች እና ታጋቾች ልውውጥ እንደ ትናንቱ እንዳይሆን እስራኤል አሳስባለች።
ሰባት ታጋቾች ከካን ዩኒስ ሲለቀቁ ፍልስጤማውያን የቀይ መስቀል ተሽከርካሪዎችን ከበው ታጋቾችን የማስረከቡ ሂደት ከአንድ ስአት በላይ ተጓቷል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በካን ዩኒስ የታየውን ትርምስ "አስደንጋጭ ትዕይት" ሲሉ የገለጹት ሲሆን፥ "ታጋቾችን ለመጉዳት የሚሞክር አካል ከባድ ዋጋ ይከፍላል" ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
ለአደራዳሪዎች ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎም የታጋቾቹ አለቃቀቅ ሰላማዊ እንደሚሆን ማረጋገጫ ማግኘታቸውን የኔታንያሁ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ሃማስ እስካሁን በካን ዩኒስ ስለተፈጠረው ነገር ምንም አስተያየት ባይሰጥም የታጋቾች አለቃቀቅ በሁለቱ ዙሮች እንደታየው ስርአት ባለው መልኩ እንዲካሄድ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።