የሀማሱ መሪ ሀኒየህ ከመሞቱ በፊት የተናገረው የመጨረሻ ቃል ምን ነበር?
ሀኒየህ የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ ዋና መቀመጫ በሚገኝባት ኳታር በትናንትናው እለት ስርአተ ቁብሩ ተፈጽሟል
'መሪ ቢሄድ ሌላ መሪ ይመጣል' ሲል ነበር ሀኒየህ ለኢራኑ ጠቅላይ መሪ ካሚኒ የተናገረው
የሀማሱ መሪ ሀኒየህ ከመሞቱ በፊት የተናገረው የመጨረሻ ቃል ምን ነበር?
የሚሞትበትን ቀን የሚያውቅ የሚመስለው ሀኒየህ በቴህራን ከመገደሉ በፊት ለኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ የተናገረው የመጨረሻ ቃል በቁርአን ውስጥ ስለሚወሱት ህይወት፣ ሞት እና ጽናት ነበር።
"ህይወት የሚሰጥም ሆነ የሚነጥቅህ አላህ ነው፤ አላህ ሁሉንም ነገር ያውቃል። 'መሪ ቢሄድ ሌላ መሪ ይመጣል'"ነበር ያለው ሀኒየህ። ሀኒየህ ይህን ከተናገረ ከጥቂት ሰአታት በኋላ ባረፈበት የእንግዳ ማረፊያ ቤት ላይ እስራኤል ሳታደርሰው አትቀርም በተባለው የሚሳይል ጥቃት ተገድሏል።
ሀኒየህ ለካሚኒ በሰጠው አስተያየት፣ በፈረንጆቹ በ1980ዎቹ በእስራኤል ላይ የተጀመረውን ዘመቻ ቅዱስ ትግል በማለት ሲሰብኩ የነበሩት የቀድሞው መሪ ሸክ አህመድ ያሲን ተጽዕኖ እንዳሳደሩበት አንጸባርቋል።
እስራኤል ያሲንን በፈረንጆቹ 2004 ብትገድላቸውም፣ ሀማስን ጠንካራ ኃይል ሆኖ ከመውጣት አላገደውም።
ሀኒየህ በ1994 ለሮይተርስ በሰጠው ቃለ ምልልስ ያሲን ፍልስጤማውያን የተወረሩባቸውን ግዛቶች ማስመለስ የሚችሉት በክንዳቸው ብቻ መሆኑን እንዳስተማሯቸው ተናግሯል።
ያሲን ፍልስጤም ተወራ ማንም ሙስሊም ተኝቶ መሞት የለበትም ይሏቸው እንደነበር ሀኒየህ ያስታውሳል።
ሀኒየህ እና ሌሎቹ የሀማስ መሪዎች፣ ለፍለስጤም ደጋፊዎች ከእስራኤል ወረራ ነጻ የሚያወጡ ተዋጊዎች እና ጉዳያቸውን በአለምአቀፍ መድረክ የሚሟገቱላቸው ናቸው። "የእስልምና ፍቅር እና መስዋትነትን እና ለጉልበተኞች እና አምባገነኖች አለመንበርከክን" ከሼክ ያሲን መማሩን ሀኒየህ ይናገራል።
ባለፈው ሚያዝያ ወር ሀዘም፣ አሚር፣ መሀመድ የተባሉት ልጆቹ እና አራት የልጅ ልጆቹ በእስራኤል የአየር ጥቃት የተገደሉበት ሀኒየህ፣ የጋዛ ጦርነት በከረረበት ወቅት ለሀማስ በአለምአቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ተሟግቷል። ሀኒየህ ሌሎች 60 የሚደርሱ ቤተሰቦቹንም በጋዛው ጦርነት ተገድዋል።
"የእኔ ልጆች ደም ከፍልስጤም ህዝብ ህጻናት የበለጠ ዋጋ የለውም...ሁሉም መስዋትነት የከፈሉ የፍልስጤም ህጻናት የእኔ ልጆች ናቸው" ነበር ያለው ሀኒየህ።
"በሰማዕታት ደም እና በተጎዱት ፍልስጤማውያን ስቃይ ለህዝቤችን ነጻነት እንፈጥራለን"ሲልም አክሏል።
"ለወራሪዎች የምንለው ይህ ደም የበለጠ መርህ እንድናጠብቅ እና ከርስታችን ያለንን ቁርኝት እንድናጠናክር ያደገናል" ብሎም ነበር።
ሀኒየህ የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ ዋና መቀመጫ በሚገኝባት ኳታር በትናንትናው እለት ስርአተ ቁብሩ ተፈጽሟል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ሀማስ በእስራኤል ላይ ከባድ የተባለ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ጦርነት እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው ጥቃት 40ሺ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ተብሏል።