ሃማስ በካይሮ ላቀረበው የተኩስ አቁም ሰነድ እስራኤል አዎንታዊ ምላሽ ትሰጥ ይሆን?
ከፍልስጤሙ ቡድን ጋር በግብጽ መዲና ለሶስት ቀናት የተካሄደው ድርድር ተጠናቋል
ግብጽ፣ ኳታርና አሜሪካ በጋዛ ከረመዳን ጾም መግቢያ በፊት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥረታቸውን ቀጥለዋል
በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ እና እስራኤላውያን ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከሃማስ ጋር በግብጽ መዲና ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ድርድር ተጠናቀቀ።
በካይሮው ድርድር እስራኤል ባለመሳተፏ ሰቆቃ ውስጥ ለሚገኙት ፍልስጤማውያን ብስራት የሚሆን ዜና አልተሰማም።
ለድርድሩ ቅርበት የነበራቸውን ሁለት ግብጻውያን ዋቢ አድርጎ አሶሼትድ ፕረስ እንደዘገበው፥ ሃማስ አዲስ የተኩስ አቁም ሰነድ አቅርቧል።
አደራዳሪዎቹ የሃማስን ሰነድ ለእስራኤል አቅርበው ድርድር የሚካሄድበት ሲሆን በቀጣይ ቀናትም የቴል አቪቭ ምላሽ ይጠበቃል።
ግብጽ፣ ኳታር እና አሜሪካ በጋዛ ከረመዳን ጾም መግቢያ በፊት ተኩስ እንዲቆም ላለፉት ሳምንታት ጥረት በማድረግ ላይ ናችው።
ለአንድ ወር በሚዘልቅ ተኩስ አቁም 40 የእስራኤል ታጋቾች እና የፍልስጤም እስረኞች እንዲለቀቁ እስራኤልና ሃማስን ለማግባባት እየተደረገ ያለው ጥረት ግን እስካሁን አልተሳካም።
የቡድኑ ቃል አቀባይ ጂሃድ ታሃ ድርድሩ ቢቀጥልም እስራኤል ተኩስ አቁማ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱም ሆነ ከጋዛ የመውጣት ምንም አይነት ፍላጎት የላትም ብለዋል።
በሶስት ቀናቱ የግብጽ ድርድር ሃማስ የተለየ ቅድመሁኔታ ስለማስቀመጡ አልተገለጸም።
ተደራዳሪዎቿን ወደ ካይሮ ያላከችው እስራኤል በሃማስ ለቀረበው የተኩስ አቁም ሰነድ አዎንታዊ ምላሽ ትሰጣለች ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው።
“ድርድሩ ተስፋ ሰጪ ነው ወይም ተስፋ አስቆራጭ ነው ማለት አልችልም፤ ግን እስካሁን በጋዛ ተኩስ ማቆም የሚያስችል ስምምነት ላይ አልተደረሰም” ብለዋል የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ።
151ኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት ህይወታቸው ያለፈ ፍልስጤማውያን ቁጥር 30 ሺህ 631 መድረሱን የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የአለማቀፍ ተቋማት የጋዛ ሰብአዊ ቀውስ በየቀኑ አሳሳቢነቱ እየከፋ መሄዱን ቢገልጹም እስራኤልና ሃማስ በኳታር አደራዳሪነት በህዳር ወር ከደረሱት ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ ለፍልስጤማውያን መጠነኛ እፎይታ የሚሰጥ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም።