ሀማስ የፖለቲካ ቢሮውን እስካሁን ከኳታር ወደ ቱርክ አለመቀየሩ ተዘገበ
ዶሃ ሀማስ ሀገሪቱን ለቆ እንዲሄድ ነግራዋለች የሚለው የሚዲያ ሪፖርትም ትክክል አይደለም ብላለች
ቱርክ እስራኤል በጋዛ እያደረሰች ያለውን ጥቃት በመቃወም ከእስራኤል ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት አቋርጣለች
ሀማስ የፖለቲካ ቢሮውን እስካሁን ወደ ቱርክ አለመቀየሩ ተዘገበ።
ሀማስ የፖለቲካ ቢሮውን ከኳታር ዶሃ ወደ ቱርክ ቀይሯል የሚለውን ሪፖርት የቱርክ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ማስተባበላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ምንጮቹ እንደገለጹት የፍልስጤሙ ታጣቂ ሀማስ አባላት በቱርክ በተለያየ ጊዜ ጉብኝት አድርገዋል።
ዶሃ ሀማስ እና እስራኤል ፈቃደኝነት እና ቁርጠኝነት እስከሚያሳዩ ድረስ በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ታጋቾች እንዲለቀቁ ስታደርግ የነበረውን የማሸማገል ጥረት ማቆሟን እንደነገረቻቸው ባለፈው ሳምንት መግለጿ ይታወሳል።
ሀማስ ሀገሪቱን ለቆ እንዲሄድ ነግራዋለች የሚለው የሚዲያ ሪፖርትም ትክክል አይደለም ብላለች ዶሃ።
ዶሃ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው፣ በኳታር፣ ግብጽ እና አሜሪካ አደራዳሪነት ለረጅም ጊዜ የተደረገው ድርድር ምንም ውጤት አለማምጣቱን ተከትሎ ነው።
ሀማስ ዘላቂ ተኩስ አቁምን እና የእስራኤልን ጦር ከጋዛ ጠቅልሎ መውጣት በቅድመ ሁኔታነት ማስቀመጡ፣ እስራኤል ደግሞ የጋዛን ደህንነት አሳልፋ መስጠት አለመፈለጓ ድርድሩ እንዳይሳካ እንቅፋት ሆኗል።
እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለውን ጦርነት በጽኑ የምታወግዘው የኔቶ አባል የሆነችው ቱርክ ሀማስን እንደ አሸባሪ ድርጅት አታየውም። የተወሰኑ የሀማስ የፖለቲካ ባለስልጣን በተደጋጋሚ ቱርክን ጎብኝተዋል።
"የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ አባላት በየጊዜው ቱርክን እየጎበኙ ነው። የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ ወደ ቱርክ ተዛውሯል የሚለው መረጃ ግን እውነታውን አያንጸባርቅም"ብለዋል ምንጮቹ።
ቱርክ እስራኤል በጋዛ እያደረሰች ያለውን ጥቃት በመቃወም ከእስራኤል ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት አቋርጣለች።
ከዚህ በተጨማሪም ሀገሪቱ ደቡብ አፍሪካ በአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በእስራኤል ላይ ያቀረበችውን የዘር ማጥፋት ክስ ደግፋ ለመከራከር ማመልከቷ ይታወሳል።