አሜሪካ ቱርክ ሀማስን እንዳታስጠጋ አስጠነቀቀች
ሀማስ ኳታር የፖለቲካ ቢሮውን ከዶሃ ወደ ቱርክ እንዲቀይር አሳውቃዋለች የሚለውን ሪፖርት አሉባልታ ነው ሲል አጣጥሎታል
አሜሪካ የቱርክ መንግስት ከሀማስ ጋር የተለመደውን አይነት ግንኙነት እንዳያደርግ ዋሽንግተን አስጠንቅቃዋለች
የሽብርተኛ ድርጀት መሪዎች ተመቻችተው መቀመጥ የለባቸውም ያለችው አሜሪካ ቱርክ ሀማስን እንዳታስጠጋው ትናንት አስጠንቅቃለች።
የተወሰኑ የሀማስ መሪዎች ከኳታር ወደ ቱርክ ሄደዋል ስለሚሉት ሪፖርቶች የተጠየቁት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ሪፖርቶቹን አላረጋገጡም፤ ነገርግን አላስተባበሉም።
ቃል አቀባዩ የቱርክ መንግስት ከሀማስ ጋር የተለመደውን አይነት ግንኙነት እንዳያደርግ ዋሽንግተን አስጠንቅቃለች ብለዋል።
ሚለር አክለውም እንደገለጹት የተወሰኑት የሀማስ መሪዎች በአሜሪካ ክስ የተመሰረተባቸው ስለሆኑ ዋሽንግተን ወደ አሜሪካ መመለስ አለባቸው ብላ ታምናለች።
"የሽብርተኛ ቡድን መሪዎች በየትኛውም ቦታ ተመችቷቸው መኖር አለባቸው ብለን አናምንም..." ሲሉ ሚለር በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ሀማስ የፖለቲካ ቢሮውን ከኳታር ዶሃ ወደ ቱርክ ቀይሯል የሚለውን ቀደም ሲል የወጣውን ሪፖርት የቱርክ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ማስተባበላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ኳታር እስራኤል እና ሀማስ ለእውነተኛ ንግግር ያላቸውን ቁርጠኝነት እስከሚያሳዩ ድረስ ተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ታጋቾች እንዲለቀቁ ለማድረግ ስታደርግ የነበረውን የማሸማገል ጥረት ባለፈው ሳምንት አቁማለች።
ዶሃ ሀማሰ ሀገሪቱን ለቆ እንዲወጣ ነግራዋለች የሚሉት የሚዲያ ሪፖርቶችም ትክክል አይደሉም ብላለች።
ምንጮቹ "የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ አባላት በየጊዜው ቱርክን እየጎበኙ ነው። የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ ወደ ቱርክ ተዛውሯል የሚለው መረጃ ግን እውነታውን አያንጸባርቅም"ብለዋል።
ሀማስም ሰኞ እለት ዘግይቶ ባወጣው መግለጫ ሪፖርቶቹን አሉባልታዎች ናቸው ሲል አጣጥሏል።
እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለውን ጦርነት በጽኑ የምታወግዘው የኔቶ አባል የሆነችው ቱርክ ሀማስን እንደ አሸባሪ ድርጅት አታየውም።
ቱርክ እስራኤል በጋዛ እያደረሰች ያለውን ጥቃት በመቃወም ከእስራኤል ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት አቋርጣለች።
ከዚህ በተጨማሪም ሀገሪቱ ደቡብ አፍሪካ በአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በእስራኤል ላይ ያቀረበችውን የዘር ማጥፋት ክስ ደግፋ ለመከራከር ማመልከቷ ይታወሳል።