የትራምፕ ዛቻ ሁኔታዎችን ከማወሳሰብ ውጭ ትርጉም የለውም - ሃማስ
የፍልስጤሙ ቡድን የእስራኤል ታጋቾች የሚለቀቁት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተፈጻሚ ከሆነ ብቻ ነው ብሏል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/11/273-161815-untitled_700x400.jpg)
ትራምፕ ሁሉም ታጋቾች እስከ ቅዳሜ ካልተለቀቁ ስምምነቱ ይፈርሳል ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል
ሃማስ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ማስፈራሪያ ዋጋ የለውም" አለ።
የቡድኑ ከፍተኛ አመራር ሳሚ አቡ ዙህሪ "ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነቱ በሁለቱም ወገን መከበር እንዳለበት ማስታወስ አለባቸው፤ ዛቻና ማስፈራሪያው ሁኔታዎችን ከማባባስ ውጭ ምንም ዋጋ አይኖረውም" ነው ያሉት።
እስራኤላውያን ታጋቾች ከጋዛ የሚወጡት በተኩስ አቁም ስምምነቱ ብቻ መሆኑንም ለሬውተርስ ተናግረዋል።
ሃማስ ስምምነቱን በሚገባ እየተገበረች አይደለም፤ በጋዛ ጥቃት እያደረሰች ነው በሚል የወቀሰው የፍልስጤሙ ሃማስ ታጋቾች የሚለቀቁበትን ጊዜ ማራዘመኑን ትናንት ገልጿል።
የእስራኤል አጋር የሆኑት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሃማስ ሁሉንም በጋዛ የሚገኙ ታጋቾች እስከ ቅዳሜ ካልለቀቀ የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዳበቃለት ይቆጠራል ብለዋል።
ታጋቾቹ እስከ ቅዳሜ እኩለ ቀን ካልተለቀቁ ግጭት ተቀስቅሶ "ድብልቅልቁ ይወጣል" ማለታቸውንም ሬውተርስ አስታውሷል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን የትራምፕን ዛቻ ከመድገም ይልቅ መለሳለስን መርጠዋል። ሁሉንም ታጋቾች ከጋዛ ለማስወጣት ስምምነቱን ተፈጻሚ ማድረጋችን እንቀጥላለን ብለዋል።
ትራምፕ ጋዛን ጠቅልሎ የመያዝና ፍልስጤማውያንን በዘላቂነት የማፈናቀል እቅዳቸውን ይፋ ባደረጉ ማግስት በእስራኤልና ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ዙሪያ የሰጡት አስተያየት ከ48 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን የቀጠፈው ጦርነት ዳግም መቀስቀሱ እንደማይቀር ያመላክታል ተብሏል።
ከጋዛ የሚወጡ ፍልስጤማውያንን ለማስፈር ከተመረጡት ሀገራት አንዷ የሆነችው ግብጽ እቅዱን ውድቅ ያደረገችው ሲሆን፥ ዮርዳኖስም ዛሬ ንጉሷ ከትራምፕ ጋር ሲመክሩ አቋሟን ታሳውቃለች ተብሎ ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ካይሮ እና አማን የጋዛ ተፈናቃዮችን የማይቀበሉ ከሆነ ከዋሽንግተን የሚደረግላቸው ድጋፍ እንደሚቋረጥ ዝተዋል።
በወታደራዊ ወረራ በተያዘ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችን በሃይል ማፈናቀል በ1949ኙ የጀኔቫ ኮንቬንሽን በጦር ወንጀልነት ተፈርጆ ታግዷል።
ፍልስጤማውያን የትራምፕ የጋዛ እቅድ "ናቅባ" ወይም "መቅሰፍት" የሚል ስያሜ የተሰጠውንና በመቶ ሺዎች ከቀያቸው የተፈናቀሉበትን የታሪክ አጋጣሚ አስታውሷቸዋል።
እስራኤል እንደ ሀገር ከመመስረቷ በፊት በተካሄደው ጦርነት ከ700 ሺህ በይ ፍልስጤማውያንን በግድ ከመኖሪያ መንደራቸው እንዲፈናቀሉ ተደርጎ በግንቦት 14 ቀን 1948 እስራኤል ነጻ ሀገር መሆኗን አውጃለች።
የእስራኤሉ የፋይናንስ ሚኒስትር ቤዛለል ስሞትሪችም ፍልስጤማውያን ለዳግም "ናቅባ" እንዲዳረጉ የሚቀሰቅስ መልዕክት አስተላልፈዋል።
"ለሃማስ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ማስተላለፍ አለብን፣ የገሃነሙን በር ለመክፈት ኤሌክትሪክ እና ውሃ እንዲሁም ሰብአዊ ድጋፍ ማቋረጥ ተገቢ ነው" ብለዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እስራኤልና ሃማስ ከእርስ በርስ መካሰስ ወጥተው የጀመሩትን የታጋቾችና እስረኞች ልውውጥ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ተፋላሚዎቹ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በሚገባ በመፈጸም በሁለተኛው ምዕራፍ ስምምነት ዙሪያ ድርድር ማድረግ እንዲጀምሩም ነው ያሳሰቡት።