የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ከሃማስ አመራሮች ጋር በቴህራን መከሩ
አያቶላህ አሊ ካሚኒ በዚሁ ወቅት ፍልስጤማውያን "አሜሪካ እና እስራኤል የትኛውንም እቅዳቸውን እንዲያሳኩ መፍቀድ የለባቸውም" ብለዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/08/273-180850-iran-hamas_700x400.jpg)
የኢራን እና ሃማስ መሪዎች የመከሩት ትራምፕ ጋዛን ለመጠቅለል እቅድ ባቀረቡ ማግስት ነው
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ በቴህራን ከሃማስ መሪዎች ጋር ተወያዩ።
የሃማስ ጊዜያዊ መሪ ካሊል አል ሃያ፣ የሃማስ ምክርቤት ሃላፊ ሞሀመድ ዳርዊሽ እና ከፍተኛ የቡድኑ አመራር ኒዛር አዋዳላህ በምክክሩ ላይ ተሳትፈዋል።
የሃማስ አመራሮች ቴህራን የተገኙት ለ1979ኙ አቢዮት 46ኛ አመት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ለማስተላለፍ መሆኑን የኢራን ብሄራዊ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ በዚሁ ወቅት ለሃማስ አመራሮች "ጽዮናዊ አገዛዙን (እስራኤል) አሸንፋችኋል፤ በርግጥ ይህ ማለት የአሜሪካ ሽንፈት ነው" ብለዋል።
ካሚኒ ለፍልስጤም ልኡክ "የእስራኤልም ሆነ የአሜሪካ የትኛውም ግብ እንዲፈጸም መፍቀድ የለባችሁም" በሚል ማሳሰባቸውንም ሬውተርስ የኢራንን ቴሌቪዥን ጠቅሶ አስነብቧል።
የሃማስ አመራሮችም በወቅታዊው የጋዛ እና ዌስትባንክ ሁኔታ ላይ ለኢራኑ ጠቅላይ መሪ ገለጻ ማድረጋቸው ተመላክቷል።
በተያያዘ 5ኛው ዙር የእስራኤልና ሃማስ የታጋቾችና እስረኞች ልውውጥ በዛሬው እለት የተካሄደ ሲሆን ሃማስ ሶስት ወንድ ታጋቾችን ለቋል። እስራኤልም 183 ፍልስጤማውያን እስረኞችን መፍታት መጀመሯ ተዘግቧል።
በ15 ወራቱ የጋዛ ጦርነት ለሃማስ ድጋፍ ስታደርግ የቆየችው ኢራን በምድሯ የሃማሱ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ መገደሉን ተከትሎ ከእስራኤል ጋር ውጥረት ውስጥ መግባቷ ይታወሳል። ሁለቱ ባላንጣዎች ሚሳኤሎችን በማዝነብ ቁጣቸውን መገላለጻቸውም አይዘነጋም።
የሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን መምጣት የሀገራቱን ውጥረት ሊያባብሰው እንደሚችል ተንታኞች ይገልጻሉ።
የትራምፕ አስተዳደር ጋዛን ለመጠቅለል ማሰቡን በገለጸ ማግስት ለእስራኤል የ7 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭን አጽድቀዋል።
ትራምፕ ፍልስጤማያንን ከጋዛ ለማስወጣት የያዙት እቅድ የ15 ወራቱን ጦርነት ዳግም ሊቀሰቅሰው እንደሚችል እየተነገረ ነው።
ፍልስጤማውያንን የምትደግፈው ኢራን ጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ካሚኒ ከሃማስ አመራሮች ጋር ሲመክሩ የትራምፕ የጋዛ እቅድ ስለመነሳቱ በኢራን ቴሌቪዥን ዘገባ አልተጠቀሰም።