ትራምፕ “ግብፅና ዮርዳኖስ የጋዛ ተፈናቃዮችን የማይቀበሉ ከሆነ የሚያገኙትን እርዳታ አቆማለሁ” ሲሉ ዛቱ
ፕሬዝዳንት ትራምፕ “ፍልስጤማውያን ከጋዛ በቋሚነት ይወገዳሉ” ሲሉ በድጋሚ አረጋግጠዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/11/252-125923-whatsapp-image-2025-02-11-at-11.58.33-am_700x400.jpeg)
ትራምፕ ጋዛን ለመቆጣጠር የያዙትን እቅድ ግብጽና ዮርዳኖስን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እየተቃወሙት ነው
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ግብፅና ዮርዳኖስ የጋዛ ተፈናቃዮችን የማይቀበሉ ከሆነ የሚያገኙትን እርዳታ አቆማለሁ” ሲሉ ዛቱ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ኃውስ እንደገቡ የጋዛ ፍርስራሽ እስኪጸዳ ድረስ ፍልስጤማውያን እንደ ግብጽ እና ዮርዳኖስ ባሉ ሀገራት እንዲጠለሉ ሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ወደ ጎረቤት ሀገራት ለማፈናቀል በያዙት እቅድ ላይ መጽናታቸውን በድጋሚ ያረጋገጡ ሲሆን፤ ለመቀበል ፍቃደኛ ያልሆኑ ሀገራትን ማስፈራታቸውን ቀጥለዋል።
ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ፍልስጤማውያን ከጋዛ በቋሚነት ይወገዳሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
ፍሊስጤማውያን መቼ ወደ ጋዛ ይመለሳሉ ተብለው የተጠየቁት ትራምፕ፤ “አይ አይመለሱም፣ ምክንያቱም የተሻለ መኖሪያ ቤት ያገኛሉ፣ በሌላ አነጋገር እኔ የማወራው ለእነሱ ቋሚ መኖሪያ ቤት ስለመገንባት ነው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ አክለውም “በርካታ ፍሊስጤማውያንን አነጋግረናል፤ ሌላ የሚኖሩበትነን ስፍራ ካገኙ ጋዛን መልቀቅ እንደሚፈልጉ ነግረውናል” ሲሉም ገልጸዋል።
“የጋዛ ፍልስጤማውያን ለስደት ተዳርገዋል፣ ተተፍቶባቸዋል እና እንደ ቆሻሻ ተቆጥረዋል” ያሉት ትራምፕ፤ “ጋዛን ለቀው መውጣት ይፈልጋሉ ነገርግን እስካሁን ሌላ አማራጭ አልተሰጣቸውም” ሲሉም አክለዋል።
የጋዛ ተፈናቃይ ፍሊስጤማውያንን ለመቀበል ፍቃደኛ ያልሆኑ ሀገራትን በተመለከተም ዶናልድ ትራምፕ “እኛም ለእነሱ የምንሰጠውን እርዳታ እናቆማለን” ሲሉ ዝተዋል።
ግብፅ እና ዮርዳኖስ ፍሊስጤማውያንን ለመቀበል ፍቃደኛ ካልሆኑ ከአሜሪካ የሚያገኙት እርዳታን ሙሉ በሙሉ እንደሚያቋርጡም ነው ትራምፕ ያስታወቁት።
የጋዛ ተፈናቃዮችን በቋሚነት እና በጊዜያዊነት እንዲያስጠልሉ ከትራምፕ ትእዛዝ የተሰጣቸው ግብጽ እና ዮርዳኖስ እቅዱን ውድቅ ያደረጉት ሲሆን፥ የፍልስጤም እና የአረብ መሪዎችም አጥብቀው ተቃውመውታል።
የዮርዳስ ንጉስ አብደላህ 2ኛ በዛሬው እለት ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትምፕ ጋር በዋሽንግተን እንደሚገናኙ የሚጠበቅ ሲሆን፤ የጋዛ ነዋሪዎችን የማፈናቀል እቅድ ዙሪያ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
የአረብ ሊግ አባል ሀገራትም በዚህ ሁለት ሳምት ውስጥ በትራምፕ እቅድ ዙሪያ በካይሮ አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምት መደረሱን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍሊስጤማውያን ወደ ፈራረሰቸው መንደራቸው እየተመሙ ይገኛሉ።
እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት ከሆነ ከአጠቃላይ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል 1.9 ሚሊየን ወይም 90 በመቶው በ15 ወሩ ጦርት ከመኖሪያቸው ለመፈናቀል ተገደዋል።