ኢራን ዲፕሎማቷ ከቢሊየነሩ መስክ ጋር በድብቅ ተወያይተዋል መባሉን አስተባበለች
ቢሊየነሩ መስክ እና በተመድ የኢራን አምባሳደር በሚስጥር መወያየታቸው ተነግሯል
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃው ሀሰትና የፈጠራ ወሬ ነው ብሎታል
ኢራን የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ኤለን መስክ እና በመንግስታቱ ድርጅት የሀገሪቱ አምባሳደር አሚር ሳይድ ኢራቫኒ በሚስጥር ተገናኝተው ተወያይተዋል መባሉን አስተባበለች።
ኒውዮርክ ታይምስን ጨምሮ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ቢሊየነሩ መስክ እና በተመድ የኢራን አምባሳደር በሚስጥር መወያየታቸው ምንጮቻቸውን ዋቢ አድርገው መዘገባቸው ይታወሳል።
ኒውዮርክ ታይምስ በተለይም የኢራን ባለስልጣናት ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው በኒውዮርክ የተካሄደው ምክክር ከአንድ ስአት በላይ የቆየ ነበር።
ምክክሩ የአሜሪካ እና ኢራንን የሻከረ ግንኙነት ለማስተካከል ያለመ እንደነበርም ነው ዘገባው የጠቀሰው።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫው፣ ቢሊየነሩ መስክ እና በተመድ የኢራን አምባሳደር መካከል ሚስጠደራዊ ውይይት ተደርጎ ነበር መባሉን በጽኑ አስተባብሏል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ፣ በኢራን የተመድ አምባሳደር እና የተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የቅርብ አማካሪ በሆኑት ኤለን መስክ እና በኢራን የተመድ አምባሳደር መካከል ተደርጓል የተባለው ውይይት ፍጹም ሀሰት ነው በማለት አስተባብለዋል።
ይህ አሜሪካ ሚዲያዎች የፈጠራ ወሬ ነው፣ ከጀርባው ምን አይነት ተልእኮ እንደለውም ግልጽ ነው ብለዋል የፈጠራ ወሬ ነው ብለውታል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ በመግለጫቸው።
የኢራን አመራሮች በተመድ የሀገሪቱ ተወካይ ለሆኑት አምባሳደር አሚር ሳይድ የውይይት ፈቃድ እንዳልሰጠም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
"በአሁኑ ወቅት አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር በኢራን ላይ የሚያራምደውን ፖሊሲ ግልጽ እስከሚያደርግ እጠበቅን ነው፣ የባይደን መንግስት ፖሊሲ ላይ በመመስረት የራሳችንን ፖሊሲ እናስተካክላለን፣ ለውይይት አሁን ጊዜው አይደለም" ብለዋል ሚኒስትሩ።
የትራምፕ ዳግም መመረጥ በኢራን ላይ “ከባድ ግፊት” ይፈጥራል ተብሎ ተሰግቷል።
የሪፐብሊካኑን ተመራጭ ፕሬዝዳንት የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን የሚያወሱ ተንታኞች ግን ትራምፕ በኢራን ላይ አዲስ ፖሊሲ የሚከተሉ አይመስልም ይላሉ።
አሜሪካን ከ2015ቱ የኢራን የኒዩክሌር ስምምነት በ2018 ያስወጡት ትራምፕ ቴህራን በስምምነቱ ተነስተውላት የነበሩ ማዕቀቦች ዳግም እንዲተገበሩ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ኢራንም የዩራኒየም ማበልጸግ ሂደቷን ከማፋጠን ባሻገር የነዳጅ የወጪ ንግዷን በእጅጉ ጨምራለች።
በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎች የምታደርገውን ድጋፍ ማጠናከሯም ለአሜሪካ ዋነኛ አጋር እስራኤል ከፍተኛ ስጋት ደቅኖ እርስ በርስ ሃይላቸውን እስከመለካካት ደርሰዋል።