ሀማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ
ለ13 ወራት ጦርነት ላይ የሚገኘው ቡድን ለቀደመው ድርድር ውድቀት እስራኤልን ተጠያቂ አድርጓል
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የሊባኖሱ የተኩስ አቁም ስምምነት ሀማስን ብቻውን የሚያስቀረው ነው ብለዋል
ሀማስ በሊባኖስ የተኩስ ስምምነት መደረጉን ተከትሎ ከእስራኤል ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል፡፡
ከአመት በላይ የዘለቀውን ጦርነት መቋጨት እንደሚፈልግ የገለጸው ቡድኑ ለበርካታ አለም አቀፍ አደራዳሪዎች አቋሙን ማሳወቁን ነው ይፋ ያደረገው።
በአሜሪካ አደራዳሪነት የተፈረመው የተኩስ አቁም ስምምነት የእስራኤል ጦር በ60 ቀናት ውስጥ ከደቡብ ሊባኖስ ለመውጣት እና የሊባኖስ ጦር ቀደም ሲል በሄዝቦላህ ቁጥጥር ስር በነበረው ድንበር ላይ እንዲሰማራ ይደነግጋል።
የሃማስ ከፍተኛ አመራር ሳሚ አቡ ዙህሪ “የሄዝቦላህ እና የእስራኤል ተኩስ አቁም ስምምነት በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት የሚያስቆም ስምምነት ላይ ለመድረስ መንገድ እንደሚጠርግ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
አቡ ዙህሪ አክለውም ሃማስ ድርድሮችን ለማከናወን እና ሀሳቦችን ለመቀበል ችግር እንደሌለበት ገልጸው ነገር ግን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦርነቱ እንዲያበቃ ፍላጎት ያላቸው አይመስሉም ነው ያሉት፡፡
አርቲ እንዳስነበበው ቡድኑ ለግብፅ፣ ቱርክ እና ኳታር የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ እና እስረኞችን ለመለዋወጥ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ የእስራኤል ጦርን ማስወጣት፣ የተፈናቀሉትን መመለስ እና እውነተኛ እና የተሟላ የእስረኞች ልውውጥን ማሳካት እንደሚገባው ነው የተገለጸው፡፡
ኔታንያሁ ባሳለፍነው ማክሰኞ ከሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ጋር ተያይዞ ባደረጉት ንግግር “ከጦርነቱ ሁለተኛው ቀን ጀምሮ ሀማስ ሄዝቦላህን ከጎኑ እንደሚፋለም ተስፋ አድርጎ ነበር፤ አሁን ሀማስ ብቻውን ቀርቷል፤ የተኩስ አቁሙ ዋና ምክንያት ግንባሩን ለመለየት እና ሀማስን ለማግለል ያለመ ነው” ብለዋል።
እስራኤል ከሄዝቦላህ ጋር መደራደሯን ተከትሎ በሀማስ ላይ የምታደርገውን ጫና እና ውግያ አጠናክራ ልትቀጥል እንደምትችል ተሰግቷል።
በኔታንያሁ ካቢኔ ውስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት አላቸው የሚባሉት የደህንነት ሚኒስትሩ ኢታማር ቤንጊቪር እና የገንዘብ ሚኒስትሩ ቤዛሌል ስሞትሪች ከሃማስ ጋር የሚደረገውን ማንኛውንም የተኩስ አቁም ይቃወማሉ፡፡
ሚኒስትሮቹ ጦርነቱ ሊጠናቀቅ የሚገባው እስራኤል ምዕራብ እየሩሳሌም ሙሉ በሙሉ ስትቆጣጠር ሊሆን ይገባል የሚል እምነትም አላቸው፡፡