አሜሪካ የፀጥታው ምክር ቤት በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ አደረገች
አሜሪካ የውሳኔ ሀሳቡን ውድቅ ያደረገችው የታጋቾችን መለቀቅ አላካተትም በሚል ነው
የባይደን አስተዳደር የጋዛን ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው አለምአቀፋዊ ጥረት ላይ ድጋሚ እንቅፋት በመሆን ከፍተኛ ትችት እየደረሰበት ነው
አሜሪካ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብትን በመጠቀም ውድቅ አደረገች።
15 አባላት ያሉት ምክር ቤቱ 10 ቋሚ ያልሆኑ አባላት ባቀረቡት የውሳኔ ሃሳብ ለ13 ወራት የዘለቀው ግጭት በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ቋሚ የተኩስ ማቆም እንዲደረግ እና ታጋቾቹ እንዲፈቱ በተናጠል ጠይቋል።
በውሳኔው ላይ የተሰጠውን ድምጽ የሻረችው አሜሪካ ምክትል አምባሳደር ሮበርት ዉድ ዋሽንግተን ታጋቾች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የሚጠይቅ የውሳኔ ሀሳብ ብቻ እንደምትደግፍ በግልጽ አቋሟን አሳውቃለች ሲሉ ገልጸዋል።
አምባሳደሩ "የጦርነቱ ዘላቂ ፍጻሜ የታጋቾቹን መለቀቅ ማካተት አለበት፤ እነዚህ ሁለት አጣዳፊ ግቦች የማይነጣጠሉ ናቸው ይህ የውሳኔ ሃሳብ ያንን አስፈላጊነት አላካተተም በዚህ ምክንያት አሜሪካ ልትደግፈው አትችልም" ብለዋል።
ዋሽንግተን የተኩስ አቁም ስምምነትን ትፈልጋለች ያሉት አምባሳደሩ ነገር ግን የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ጽሁፍ ለፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ ወደ ድርድር ጠረጴዛ መመለስ አያስፈልግም የሚል አደገኛ መልዕክት ያስተላለፈ ነበር ነው ያሉት።
የውሳኔ ሀሳቡን ያቀረቡት የምክር ቤቱ ተለዋዋጭ 10 አባላት አልጄሪያ፣ ኢኳዶር፣ ጉያና፣ ጃፓን፣ ማልታ፣ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ስሎቬኒያ እና ስዊዘርላንድ የውሳኔ ሃሳቡ ውድቅ በመደረጉ በአሜሪካ ላይ ትችት ሰንዝረዋል።
የማልታ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አምባሳደር ቫኔሳ ከድምጽ ሂደቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር “ይህ ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ በመሻር መብት ምክንያት በድጋሚ ዓለም አቀፍ ሰላምን እና ደህንነትን የማስጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉ በጣም እናዝናለን” ብለዋል።
የቻይናው አምባሳደር ፉ ኮንግ በበኩላቸው “አሜሪካ እስራኤልን ለመጠበቅ ድምጿን በሰጠች ቁጥር በጋዛ የሚገደሉት ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ፤ከማስመሰል እንቅልፍ ከመነሳታቸው በፊት ስንት ሰዎች መሞት አለባቸው?" ሲሉ ጠይቀዋል።
በጥር 20 ከስልጣን የሚለቁት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለእስራኤል ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ እና የጦር መሳርያ ድጋፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም።