ሃማስ በጋዛ የሚገኙ አሜሪካውን ታጋቾችን ለመልቀቅ ተስማማ
የፍልስጤሙ ቡድን ሁለተኛው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ድርድር እንዲጀምር አደራዳሪዎች ላቀረቡት ምክረሃሳብ አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱንም አስታውቋል

አሜሪካ በቅርቡ በሽብር ከፈረጀችው ሃማስ አመራሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የቀጥታ ንግግር ማድረጓ ይታወሳል
ሃማስ የአሜሪካ እና እስራኤል ጥምር ዜግነት ያለውን ታጋች ለመልቀቅ መስማማቱን አስታወቀ።
በጋዛ ህይወታቸው ያለፈ አራት አሜሪካውያን ታጋቾን አስከሬን እንደሚያስረክም ነው በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ የጠቆመው።
በጋዛ የሚገኘውን የመጨረሻ የአሜሪካ ዜግነት ያለውን ታጋች እና የአራት አሜሪካውያንን አስከሬን ለመልቀቅ ግን እስራኤል ከሁለት ሳምንት በፊት የዘጋቻቸውን የእርዳታ መተላለፊያዎች መክፈት አለባት ብሏል።
ሃማስ በቅርቡ በሽብር ከፈረጀችው አሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የቀጥታ ንግግር ማድረጉ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የታጋቾችን ጉዳይ በተለመከተ ልዩ መልዕክተኛ አድርገው የሾሟቸው አዳም ቦህለር በዶሃ ተካሂዷል ስለተባለው ሚስጢራዊ ንግግር ማብራሪያ መስጠታቸውም አይዘነጋም።
የፍልስጤሙ ቡድን በጋዛ ታግቶ የሚገኘው የ21 አመቱ ኤዳን አሌክሳንደርም ሆነ የአራት የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ታጋቾች አስከሬን ስለሚለቀቁበት ጊዜ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠም።
እስራኤልና ሃማስ በሶስት ምዕራፍ የሚተገበር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰው ከፈረንጆቹ ጥር 19 ጀምሮ ተፈጻሚ ማድረግ ጀምረው የመጀመሪያው ምዕራፍ ከሁለት ሳምንት በፊት ተጠናቋል።
ለ42 ናት በቆየው የመጀመሪያ ምዕራፍ ሃማስ 33 እስራኤላውያን እና 5 ታይላንዳውያን ታጋቾችኝ፤ እስራኤል ደግሞ 2 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ቢለቁም በሁለተኛው ምዕራፍ ዙሪያ እስካሁን ከስምምነት አልደረሱም።
እስራኤል ለ42 ቀናት ተኩስ አቁሙን ለማራዘም ሃሳብ አቅርባለች።
ሃማስ ግን በስምምነቱ መሰረት በሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ዙሪያ ለመደራደር እንጂ የተኩስ አቁም ማራዘሚያን እንደማይቀበል ማሳወቁን ሬውተርስ በዘገባው አስታውሷል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ሃማስ ሁሉንም ታጋቾች መልቀቅ፤ እስራኤል ደግሞ ከጋዛ ወታደሮቿን ማስወጣት እንዳለባት በአሜሪካ አደራዳሪነት በተደረሰው የመጀመሪያ ስምምነት መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር ሃማስ የተኩስ አቁም ማራዘሚያ ሃሳቡን ባለመቀበሉ ወደ ጋዛ ምንም አይነት የሰብአዊ ድጋፍ እንዳይገባ አድርጓል።
አሜሪካ፣ ግብጽ እና ኳታር ሁለቱ ተፋላሚዎች ልዩነታቸውን እንዲያጠቡና ድርድር እንዲጀምሩ ጥረታቸውን መቀጠላቸውን አስታውቀዋል።
ሃማስ በትናንትናው እለትም በሁለተኛው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ላይ ድርድር እንዲጀመር የሚጠይቅ ደብዳቤ ከአደራዳሪዎች እንደደረሰው የቡድኑ ቃል አቀባይ አብደል ላቲፍ አል ቃኑአ ለሬውተርስ ተናግረዋል።ለቀረበው የድርድር ምክረሃሳብ "አዎንታዊ" ምላሽ መስጠቱንም ነው ያብራሩት።