አሜሪካ እና እስራኤል ፍልስጤማውያን እንዲሰፍሩባቸው የመረጧቸው የአፍሪካ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፍልስጤማውያን ከጋዛ በሃይል እንዲወጡ አይደረጉም ቢሉም የመጀመሪያ እቅዳቸውን እንደገፉበት ተገልጿል

ዋሽንግተን እና ቴል አቪቭ ከጋዛ የሚወጡ ፍልስጤማውያንን ለሚቀበሉ ሀገራት የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ ቃል ገብተዋል
አሜሪካ እና እስራኤል ከጋዛ እንዲወጡ የሚደረጉ ፍልስጤማውያንን እንዲያሰፍሩ የአፍሪካ ሀገራት መንግስታትን ማነጋገራቸው ተገለጸ።
አሶሼትድ ፕረስ የእስራኤልና አሜሪካ ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንዳስነበበው ንግግሩ የተደረገው ከሱዳን፣ ሶማሊያ እና ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ባለስልጣናት ጋር ነው።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋዛን ለመቆጣጠርና ለማልማት ያቀረቡት እቅድ ከፍተኛ ተቃውሞን ማስተናገዱን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ፍልስጤማውያን ከጋዛ በሃይል እንዲወጡ አይደረጉም ማለታቸው ይታወሳል።
ዋይትሃውስ ግን ትራምፕ "በራዕያቸው እንደገፉበት ነው" ብሏል።
ከባለፈው ወር ጀምሮም ከሁለቱ ሀገራት እና ሶማሊያ እንደ ሉአላዊ ግዛቷ ከምትቆጥራት ሶማሊላንድ ጋር ሚስጢራዊ ምክክር መደረጉን ነው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአሜሪካ እና እስራኤል ባለስልጣናት ለአሶሼትድ ፕረስ የተናገሩት።
ዋሽንግተን እና ቴል አቪቭ ከጋዛ የሚወጡ ፍልስጤማውያንን ለሚቀበሉ ሀገራት የፋይናንስ፣ የዲፕሎማሲያዊ እና ደህንነት ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋልም ተብሏል።
ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው አራት የአረብ ሀገራት ከእስራኤል ጋር "የአብርሃም ስምምነት" እንዲፈራረሙ ሲያደርጉ የተጠቀሙትን ስልት በድጋሚ ለመተግበር እየተንቀሳቀሱ መሆኑም ተገልጿል።
የፍልስጤማውያኑን ከጋዛ መፈናቀል የሚደግፉት የእስራኤል የፋይናንስ ሚኒስትር ቤዛለል ስሞትሪች ከሰሞኑ በሰጡት አስተያየት እስራኤል ፍልስጤማውያኑን ሊያሰፍሩ የሚችሉ ሀገራትን እየለየች ነው ማለታቸው ይታወሳል።
በእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር ስር "በጣም ግዙፍ የስደተኞች ጉዳይ ክፍል" እየተቋቋመ ነው ማለታቸውም የትራምፕ እቅድን ተፈጻሚ ለማድረግ እንቅስቃሴው መቀጠሉን አመላክቷል።
ፍልስጤማውያንን እንዲቀበሉ በአሜሪካ እና እስራኤል ጥያቄ የቀረበላቸው ሀገራት ምን ምላሽ ሰጡ?
ሱዳን
በፈረንጆቹ 2020 ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን በአብርሃም ስምምነት ለማደስ ከተስማሙት አራት ሀገራት አንዷ የሆነችው ሱዳን ለፍልስጤማውያን መስፈሪያ ቦታ እንዲሰጡ ጥያቄ ከቀረበላቸው ሀገራት አንዷ ናት።
በ2020ው ስምምነት መሰረት አሜሪካ ካርቱምን ሽብርተኝነትን በመንግስት ደረጃ ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር አስወጥታ አለማቀፍ ብድር እንድታገኝ ብታደርግም በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከቴል አቪቭ ጋር ግንኙነቷን በሚፈለገው ደረጃ እንዳታድስ አድርጓታል።
አሜሪካ እና እስራኤል ፍልስጤማውያንን በጦርነት ውስጥ ወደምትገኘው ሱዳን እንዲያመሩ የሚያቀርቡት ሃሳብ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደሚያስተናግድ ቢጠበቅም ለካርቱም መንግስት የብድር ስረዛ፣ የጦር መሳሪያ፣ ቴክኖሎጂ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ማማለያዎችን ሊያቀርቡ ይችላሉ።
ሁለት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሱዳን ባለስልጣናት የትራምፕ አስተዳደር ወታደራዊው መንግስት ፍልስጤማውያንን እንዲቀበል ማነጋገሩን አረጋግጠዋል።
የሱዳን ጦር የፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ)ን ለመምታት ድጋፍ እናደርጋላችኋለን በሚል ለቀረበለት ሃሳብ አሉታዊ ምላሽ መስጠቱንም ነው ያነሱት።
የሱዳን ጦር አዛዥ ጀነራል አብደልፈታህ አልቡርሃን ባለፈው ወር በአረብ ሀገራት መሪዎች በካይሮ ሲመክሩ ፍልስጤማውያንን ከቀያቸው የማፈናቀል እቅድ "ምንም የዳቦ ስም ቢሰጠው ተቀባይነት የለውም" ማለታቸው ይታወሳል።
ሶማሊላንድ
ሶማሊላንድ ከ30 አመት በፊት ከሶማሊያ ከተገነጠለች በኋላ የራሷን መንግስት፣ ጦር እና መገበያያ ገንዘብ በመጠቀም እንደ ሉአላዊ ሀገር ብትንቀሳቀስም እስካሁን ሀገራት እውቅና አልሰጧትም።
የሶማሊላንድ አዲሱ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሀመድ አብዱላህ አለማቀፍ እውቅና የማግኘት ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጡት እንደሆነ ተናግረዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ለሶማሊላንድ እውቅና በመስጠት ፍልስጤማውያንን በሀገሪቱ የማስፈር ንግግር ስለማድረጉ አሶሼትድ ፕረስ የአሜሪካ ባለስልጣንን ጠቅሶ አስነብቧል።
የሃርጌሳ ሹማምንት ግን ሚስጢራዊ ነው የተባለውን ምክክር እንደማያውቁት መናገራቸውን ዘገባው አክሏል።
ሶማሊያ
የምስራቅ አፍሪካዋ ሀገር ዜጎቿ በፍስልጤማውያን ላይ የሚፈጸም በደል ይቆም ዘንድ በአደባባይ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ በማድረግ ድጋፏን በተደጋጋሚ አሳይታለች።
ሞቃዲሾ የትራምፕን ጋዛን የመጠቅለል እቅድ ውድቅ ያደረገው የአረብ ሀገራት ጉባኤ አካልም ነበረች።
በመሆኑም ፍልስጤማውያንን ለማስፈር ከአሜሪካ እና እስራኤል የቀረበላትን ጥያቄ የመቀበሏ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ተብሏል። በምላሹ የሚቀርብላት ድጋፍ ግን አቋሟን ሊያስቀይራትም ይችላል።
አሶሼትድ ፕረስ ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሶማሊያ ባለስልጣን ግን ሞቃዲሾ ከጋዛ የሚፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን በምታስጠልልበት ሁኔታ የተደረገ ምክክር የለም ብለዋል።