ትራምፕ ከአውሮፓ በሚገቡ የአልኮል ምርቶች ላይ የ200 በመቶ ታሪፍ ለመጣል ዛቱ
የአውሮፓ ህብረት በአሜሪካ ውስኪ ምርት ላይ የ50 በመቶ ታሪፍ ለመጣል ያሳለፈውን ውሳኔ በፍጥነት እንዲሽርም አሳስበዋል

አሜሪካ ባለፈው አመት 4.9 ቢሊየን ዩሮ የሚያወጣ ወይን ከአውሮፓ ሀገራት አስገብታለች
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአውሮፓ ሀገራት በሚገቡ የወይን እና ሌሎች የአልኮል መጠጦች ላይ የ200 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ ተናገሩ።
ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የራሳቸው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በለጠፉት መልዕክት "የአውሮፓ ህብረት በአሜሪካ ላይ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ከፍተኛ ታሪፍ ይጥላል፤ በአሜሪካ ውስኪ ላይ ለመጣል የወሰነው የ50 በመቶ ታሪፍም የዚህ ማሳያ ነው" ሲሉ ወቅሰዋል።
በውስኪ ላይ ሊጣል የታሰበው ታሪፍ በፍጥነት ካልተነሳም ከፈረንሳይና ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሁሉም የወይን፣ ሻምፓኝ እና ሌሎች የአልኮል ምርቶች ላይ የ200 ፐርሰንት ታሪፍ ለመጣል ዝተዋል።
በአውሮፓ የአልኮል ምርቶች ላይ የሚጣለው ታሪፍ በአሜሪካ በወይን እኛ ሻምፓኝ ንግድ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ትልቅ አበርክቶ እንዳለውም ነው የጠቆሙት።
የአውሮፓ የስታስቲክስ ተቋም "ዩሮስታት" መረጃ እንደሚያሳየው የአውሮፓ ሀገራት ባለፈው አመት 4.9 ቢሊየን ዩሮ የሚያወጣ ወይን ወደ አሜሪካ ልከዋል።
ከአውሮፓ ጠቅላላ የወይን የወጪ ንግድ አሜሪካ 29 በመቶውን ድርሻ ትይዛለች። ፈረንሳይ እና ጣሊያን በወይን ሽያጩ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።
በካናዳ፣ ሜክሲኮ እና ቻይና ላይ ታሪፍን መሳሪያ አድርገው የንግድ ጦርነት ያስጀመሩት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአውሮፓ ህብረትንም አካተውታል።
ትራምፕ ከአውሮፓ በሚገቡ የብረትና አልሙኒየም ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ ትናንት ይፋ አድርገዋል።
የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች፣ አልባሳት፣ የቤት ውስጥ መገልገያ መሳሪያዎች፣ የበሬ ስጋ፣ እንቁላል፣ የወተት ተዋጽኦ ውጤቶች፣ ስኳር እና አትክልቶች ታሪፍ የሚጣልባቸው ናቸው።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በሰጠው ምላሽም 26 ቢሊየን ዩሮ በሚያወጡ የአሜሪካ ምርቶች ላይ ከቀጣይ ወር ጀምሮ ታሪፍ እንደሚጥል ማሳወቁን ሬውተርስ ዘግቧል።
ህብረቱ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን እንዳሳወቀ ትራምፕ ይፋ ያደረጉት የ200 በመቶ ታሪፍ የንግድ ጦርነቱን እንዳያባብሰው ስጋት ፈጥሯል።