የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ የአሜሪካን እንደራደር ጥያቄ ውድቅ አደረጉ
ጠቅላይ መሪው በኒዩክሌር ፕሮግራም ዙሪያ ከትራምፕ የተላከላቸው ደብዳቤ በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በኩል ደርሷቸዋል

ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ወደ ድርድር ካልተመለሰች ወታደራዊ አማራጭን እንደሚጠቀሙ ዝተዋል
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ በሀገሪቱ የኒዩክሌር ፕሮግራም ጉዳይ ለመደራደር ከአሜሪካ የቀረበላቸውን ጥያቄ እንደማይቀበሉ አስታወቁ፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጠቅላይ መሪው ደብዳቤ መላካቸውን ገልጸው ነበር፡፡
በዚህ ንግግራቸው ላይ “ኢራን ሁለት አማራጭ አላት ወይ ለድርድር ፈቃደኛ መሆን አልያም ወታደራዊ እርምጃን መቀበል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህን ተከትሎ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዤሽኪያን በትላንትናው ዕለት “ከሚያስፈራራን አካል ጋር አንደራደርም፤ ትራምፕ የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ” ሲሉ ማናገራቸው ይታወሳል፡፡
ትራምፕ ለኢራን ከፍተኛ መሪዎች የጻፉትን ደብዳቤ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ፕሬዝዳንት ዲፕሎማሲያዊ አማካሪ አንዋር ጋርጋሽ ለኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አርጋቺ በትላንትናው ዕለት አስረክበዋል።
የአረብ ኤሜሬትሱ ልዑክ ደብዳቤውን ለኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባስረከቡበት ተመሳሳይ ወቅት ከዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር ውይይት ላይ የነበሩት የኢራን ጠቅላይ መሪ የአሜሪካን የእንደራደር ጥያቄ “አታላይ” ሲሉ ጠርተውታል፡፡
ከትራምፕ የተላከውን ደብዳቤ እንዳልተመለከቱት የገለጹ ሃሚኒ "የድርድር ስምምነት ውልን እንደማያከብሩ ስናውቅ መደራደር ምን ዋጋ አለው? ስለዚህ ለመደራደር መጋበዙ ማታለል ካልሆነ ጥቅም የለውም" ሲሉ መናገራቸውን የሀገሪቱ መንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ከ2015ቱ የኢራን የኒዩክሌር ስምምነት በመውጣት የኢራንን ኢኮኖሚ ያሽመደመደ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣላቸው ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ስምምነቱ ኢራን ለሽብርተኞች የምታደርገውን ድጋፍ እንድታጠናክር አግዟታል ያሉት ፕሬዝዳንቱ አዲስ ድርድር እንዲካሄድ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ትራምፕ ቴህራን ወደ ድርድር ጠረጴዛው የማትመለስ ከሆነ ማዕቀቦችን ከማጥበቅ እስከ ወታደራዊ እርምጃ ድረስ ሊወስዱ እንደሚችሉ እየዛቱ ነው፡፡
በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከሀገሪቱ ጋር ለመነጋገር ክፍት መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተመሳሳይ ጊዜ “ኢራንን ከአለም ኢኮኖሚ በማግለል ወደ ወጭ የምትልከውን ምርት መጠን ወደ ዜሮ አወርደዋለሁ” ብለዋል፡፡
በኢራን ጉዳይ የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ አካል የሆኑት አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ኢራንን በማስፈራራት ወደ ድርድር ማምጣት አይቻልም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
“የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መገንባት ብንፈልግ አሜሪካ ልታስቆመን አትችልም፤ ነገር ግን እኛ ራሳችን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ አንፈልግም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአለም አቀፉ የአቶሚክ ሀይል ኤጄንሲ የኢራን የዩራኒየም የጥራት ደረጃ 60 በመቶ መድረሱን ባለፈው ወር መገባደጃ ላይ ይፋ ያደረገ ሲሆን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ለመገንባት የሚያስፈልገው የዩራኒየም ደረጃ 90 በመቶ ነው፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ከኢራን ጋር ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ የምትገኘው እስራኤል በበኩሏ ኢራን አሜሪካ ባቀረበችው እቅድ የኒዩክሌር ፕሮግራሟን ለመቀነስ ካልተስማማች በማብላያ ጣቢያዎቿ ላይ ጥቃት እንደምትሰነዝር መዛቷ ይታወቃል፡፡