ርቀቱን ሳይጠብቅ ፊት ለፊቱ ወዳለው መኪና በጣም ተጠግቶ የነዳው አሽከርካሪ 110 ሺህ ዶላር ተቀጣ
የቅጣት ገንዘቡ ግለሰቡ ሲነዳው ከነበረው መኪና ዋጋ በእጥፍ የሚበልጥ ነው ተብሏል

በስዊዘርላንድ የትራፊክ ህግ የጣሰ ሰው በሚያገኘው ገቢ መጠን ተሰልቶ የሚቀጣው
በስዊዘርላንድ ርቀቱን ሳይጠብቅ ፊት ለፊቱ ወዳለው መኪና በጣም ተጠግቶ የነዳው አሽከርካሪ 110 ሺህ ዶላር ተቀጣ።
አውሮፓዊቷ ሀገር ስዊዘርላንድ ጠንከር ባሉ እና አስገራሚ የትፊክ ህግና ቅጣቶች የምትታወቅ ሲሆን፤ ከሰሞኑ የትራፊክ ህግ የጣሰ ግለሰብ ላይ የተጣለው ቅጣትም በርካቶችን አስገርሟል።
በስዊዘርላንድ የትራፊክ ህግ የጣሰ ሰው በሚያገኘው ገቢ መጠን ተሰልቶ የሚቀጣ ሲሆን፤ የገንዘብ ቅጣቱ መጠን ሀብታም በመሆኑ ሰዎች ላይ ባላቸው ገቢ መጠን ከፍ እያለ እንደሚሄድ ተነግሯል።
በሀገሪቱ ህግ መሰረት አንድ ሰው ሀብታም በሆነ መጠን የሚከፍለው የቅጣት ገንዘብ እየጨመረ የሚሄድ ሲሆን፤ እንዳንዴ የገንዘብ ቅጣቶቹ የትራፊክ ህግ የጣሰው ሰው ከሚያሽከረክረው መኪና ዋጋ ሲበልጥም ይታያል።
በቅርቡ ከስዊዘርላንድ የተሰማው ዜና ይህንኑ የሚያረጋግጥ ሲሆን፤ ከፊት ለፊቱ ያለውን መኪና በጣም ተጠግቶ ሲያሽከረክር የተገኘው የህግ ባለሙያ 110 ሺህ ዶላር ወይም 14 ሚሊየን ብር መቀጣቱ ተሰምቷል።
የ58 ዓመቱ ስዊዘርላንዳዊ የህግ ባለሙያ በፈረንጆቹ 2023 ላይ ነበር ከፊት ለፊቱ የነበረውን መኪና ከተፈቀደው ርቀት ውጪ በጣም ተጠግቶ በመንዳት ላይ እያለ በፖሊስ የተያዘው።
ይህንን ተከትሎም የስዊዘርላንድ ፍርድ ቤት በግዴለሽነት የተከሰሰውን አሽከርካሪ ዓመታዊ ገቢው የሆነው 1.8 ሚሊየን ዶላር ላይ ተሰልቶ 110 ሺህ ዶላር እንዲቀጣ የወሰነው።
አሸከርካሪው ርቀትን ጠብቆ ማሽከርከር ላይ ስዊዘርላንድ ግልጽ ህግ የላትም፤ ስለዚህ ቅጣቱ ተገቢ አይደለም በሚል ይግባኝ ጠይቆ ነበር።
የስዊዘርላንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባሳለፍነው ወር በዋለው ችሎት የመጀመሪያውን ውሳኔ በማጽናት አሸከርሪው 109 ሺህ 500 ዶላር እንዲከፍል ወስኖበታል።
ግልሰቡ የተጣለበት የገንዘብ ቅጣት በወቅቱ ይነዳ ከነበረው “BMW 540d ሴዳን” መኪና ዋጋ በእጥፍ የመበልጥ መሆኑ በርካቶችን አስገርሟል።