ሀማስ በመጀመሪያው ዙር የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት የመጨረሻዎቹን ስድስት ታጋቾች ለቀቀ
በሀማስ እየተመራ ያለው ታጋቾች ወደ መድረክ እንዲወጡና የተወሰኑት በህዝብ ፊት እንዲናገሩ የሚያደርገው ስነስርአት ተመድን ጨምሮ በርካቶች ትችት እያቀረቡበት ነው

ሀማስ ግን ስነስርዓቱ የፍልስጤማውያንን አንድነት ለማሳየት ነው በማለት ትችቱን አይቀበልም
ሀማስ ከእስራኤል ጋር በደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት ይለቀቃሉ የተለባሉትን የመጨረሻዎቹን በህይወት ያሉ ስድስት ታጋቾችን በፍልስጤማውያን እስረኞች በመለወጥ በዛሬው እለት ለቋል።
የሀማስ ታጣቂዎች ጥቅምት 7፣2023 የደቡብ እስራኤልን ድንበር ጥሰው ጥቃት በፈጸሙበት ወቅት የተያዙት የ27 አመቱ ኢሊያ ኮሄን፣ የ27 ኦመር ሼም ቶቭ፣ የ23 አመቱ ኦመር ወንከርት በማዕከላዊ ጋዛ ለቀይ መስቀል ተላልፈው ከተሰጡ በኋላ የእስራኤል ጦር ወደላበት ተልከዋል።
በደርዘን የሚቆጠሩ አውቶማቲክ ጠብመንጃ የታጣቁ የሀማስ ታጣቂዎች ርክክቡን ለማየት በተሰበሰበ ህዝብ ፊት የተጎሳቆሉ ታጋቾችን አጅበው ታይተዋል።
ሌሎቹ ሁለቱ የ40 አመቱ ታል ሻሎም፣ የ39 አመቱ ቤተ-እስራኤላዊ አይሁድ አቬራ መንግስቱ ደግሞ በሀማስ ታጣቂዎች ወደ መድረክ ከወጡ በኋላ በደቡባዊ ጋዛ ራፋ ለቀይ መስቀል ተላልፈው የተሰጥተዋል።
አል ሰይድና መንግስቱ ወደ ጋዛ ባልታወቀ ሁኔታ ከገቡ በኃላ ለአስርት አመታት ያህል በሀማስ ተይዘው ቆይተዋል።
በሀማስ እየተመራ ያለው ታጋቾች ወደ መድረክ እንዲወጡና የተወሰኑት በህዝብ ፊት እንዲናገሩ የሚያደርገው ስነስርአት ተመድን ጨምሮ በርካቶች "ታጋችን በማንገላታት" ትችት እያቀረቡበት ነው። ሀማስ ግን ስነስርዓቱ የፍልስጤማውያንን አንድነት ለማሳየት ነው በማለት ትችቱን አይቀበልም።
ሀማስ ስድስተኛውን ታጋች ሂሻም አልሰይድን ያለ ህዝባዊ ስነስርአት በጋዛ ከተማ ለቀይ መስቀል አስረክቧል።
እስራኤል በምትኩ 602 የሚሆኑ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትለቃለች ተብሏል። ሀማስ እንደገለጸው ከሚለቀቁት ውስጥ በጋዛ በእስራኤል ጦር ተይዘው የታሰሩ 4ዐዐ ፍልስጤማውያንና በደርዘን የሚቆጠሩ ፍርደኞች ይገኙበታል።
በሀማስ እና በእስራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በተሳሳተ አስከሬን ምክንያት የመናድ አደጋ ገጥሞት ነበር። ሀማስ ከልጆቿ ጋር ታግታ ተወሳዳ የሞተችው የቢባስ አስከሬን ነው ብሎ ለእስራኤል ማስረከቡና እስራኤል የእሷ አለመሆኑን ማረጋገጧ ውጦረት ፈጥሮ ነበር። ነገርግን ሀማስ ቤተሰቦቿ የቢባስ ነው ያሉትን አስከሬን ባለፈው አርብ እለት በማስረከቡ ውዝግቡ ተፈትቷል።
እስራኤልና ሀማስ፣ ሁሉም ታጋቾች በሚለቀቁበት፣ ዘላቂ ተኩስ አቁም በሚደረግበትና የእስራኤል ጦር ከጋዛ ጠቅልሎ በሚወጣበት ጉዳይ ሁለተኛ ዙር የተኩስ ከቁም ድርድር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።