አሜሪካ የዩክሬንን የስታርሊንክ የኢንተርኔት አገልግሎት ልታቋርጥ እንደምትችል ተገለጸ
ስታርሊንክ በጦርነት ለፈራረሰችው ዩክሬንና ጦሯ ወሳኝ የኢንተርኔት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ዩክሬን በወሳኝ ማዕድናት ዙሪያ ስምምነት ላይ የማትደርስ ከሆነ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንደሚቋረጥባት የአሜሪካ ተደራዳሪዎች ነግረዋታል ተብሏል
አሜሪካ የዩክሬንን የስታርሊንክ የኢንተርኔት አገልግሎት ልታቋርጥ እንደምትችል ተገለጸ።
የአሜሪካ ተደራዳሪዎች ወሳኝ ማዕድናትን ለማግኘት በኪቭ ላይ እያደረጉ ያሉት ጫና የኢሎን መስኩ የሳተላይት ኢንተርኔት አገልግሎት ሊቋረጥባት ይችላል የሚል ስጋት እንዲጨምር ማድረጉን ሮይተርስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰን ያቀረቡትን የብርቅ ወይም ውድ ማዕድናት እቅድ ውድቅ ካደረጉ በኋላ የዩክሬን የስታርሊንክ ተጠቃማነት ጉዳይ በአሜሪካ በዩክሬን ባለስልጣናት የመወያያ ርዕስ ሆኗል ብሏል ዘገባው።
ስታርሊንክ በጦርነት ለፈራረሰችው ዩክሬንና ጦሯ ወሳኝ የኢንተርኔት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ባለፈው ሀሙስ እለት በአሜሪካ የዩክሬን ልዩ መልእክተኛ ኬይት ኬሎግና በፕሬዝደንት ዘለንስኪ መካካል በተደረገው ውይይት ወቅትም ጉዳዩ ተነስቷል።
በውይይቱ ወቅት ዩክሬን በወሳኝ ማዕድናት ዙሪያ ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ የማትደርስ ከሆነ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንደሚቋረጥባት ተነግሯታል ተብሏል።
"ዩክሬን ስታርሊንክ እየተጠቀመች ነው፤ እንደ ሰሜን ኮከባቸው ነው የሚያዩት። ስታርሊንክን ማጣት ከባድ ችግር ያስከትላል" ሲሉ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ሮይተርስ ያናገራቸው ምንጭ ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ዩክሬን አሜሪካ በጦርነቱ ወቅት ላደረገችላት ድጋፍ 500 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ውድ ማዕድናት እንድታቀርብ ያቀረቡትን ጥያቄ ዘለንስኪ የደህንነት ዋስትናን ያረጋገጠ አይደለም በማለት ውድቅ አድርገውታል።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ በትናንትናው እለት የአሜሪካ የዩክሬን ቡድኖች ስምምነት ላይ ለመድረስ እየሰሩ መሆናቸው ሲገለጹ ትራምፕ ስምምነቱ በቅርቡ ይፈረማል ብለዋል።
መስክ በ100 ዎች የሚቅጠሩ የስታርሊንክ ተርሚናሎችን በማቋቋም ሩሲያ በየካቲት 2022 በጀመረችው ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ የወደሙ የግንኙነት አገልግሎትን መተተካት በዩክሬን ጀግና ተብሎ ተወድሶ ነበር።
የስታርሊንክ ኢንተርኔት አገልግሎት ኪቭ ጦርነቱን በአግባቡ እንድትመራ ረድቷታል ተብሏል።