ሃማስ ለረቂቅ የተኩስ አቁም ስምምነቱ “አዎንታዊ ምላሽ” ሰጥቷል - ኳታር
የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አልታኒ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር መክረዋል
የፍልስጤሙ ቡድን በጋዛ ሙሉ በሙሉ ተኩስ እንዲቆምና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል
ሃማስ ለአዲሱ ረቂቅ የተኩስ አቁም ስምምነት “አዎንታዊ ምላሽ” ሰጥቷል አሉ የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱልራህማን አልታኒ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዶሃ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው የፍልስጤሙ ቡድን ለስምምነቱ ምላሽ መስጠቱን የገለጹት።
እስራኤልና ሃማስን በማደራደር ለአንድ ሳምንት የዘለቀ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ያደረገችው ኳታር ሃማስ ስላስቀመጣቸው ዝርዝር ቅድመ ሁኔታዎች አልገለጸችም።
ይሁን እንጂ ቡድኑ ባወጣው መግለጫ በጋዛ ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላቂ ግጭት ማቆም እንዲኖርና እስራኤል ጥቃቷን ሙሉ በሙሉ እንድታቆም እንደሚፈልግ አስታውቋል።
የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱልራህማን አልታኒ በመግለጫቸው ሃማስ በረቂቅ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ የተወሰኑ አስተያየቶችና ቅራኔዎች እንዳሉት መግለጻቸውን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
በግብጽ፣ ኳታር እና ሳኡዲ አረቢያ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው እስራኤል የገቡት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሃማስ ባነሳቸው ቅድመ ሁኔታዎች ዙሪያ ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩ ተናግረዋል።
ሃማስ “የፍልስጤሙ ማንዴላ” ተብሎ የሚጠራውን ማርዋን ባርጉቲን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ በእስራኤል እስር ቤቶች የሚገኙ ፍልስጤማውያን እንዲለቀቁ መጠየቁ ይታወሳል።
በካን ዩኒስና ፍልስጤማውያን በተጠለሉበት የራፋህ መተላለፊያ ጥቃቷን ያጠናከረችው እስራኤል ከ130 በላይ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ያግዛል የተባለውን የተኩስ አቁም ስምምነት ለመፈረም በሃማስ በኩል የቀረቡ ቅድመሁኔታዎች ለማሟላት ፍቃደኛ ትሆናለች ተብሎ አይጠበቅም።
የፍልስጤማ ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው 124ኛ ቀኑን በያዘው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 27 ሺህ 585 ደርሷል።