ሩሲያ "ተቀባይነት የሌለው" አስተያየት የሰጡትን የእስራኤል አምባሳደር ጠርታ እንደምታናግር ገለጸች
አምባሳደሯ በቃ ለምልልሱ ሩሲያ ለፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ የቅርብ ወዳጅ ነችም ብለዋል
የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ መንስኤ የአሜሪካ የተሳሳተ ፖሊሲ ነው ብላ የምታስበው ሩሲያ፣ በጋዛ ተኩስ እንዲቆም እና ሰላማዊ መፍትሄ እንዲመጣ ትፈልጋለች
ሩሲያ "ተቀባይነት የሌለው" አስተያየት የሰጡትን የእስራኤል አምባሳደር ጠርታ ልታናግር መሆኑን ገለጸች።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስራኤል አምባሳደር ሲሞና ሀርል ፐሪል በቃለ መጠይቅ ወቅት ሰጥተውታል በተባለው "ተቀባይነት የሌለው አስተያየት" ምክንያት ጠርቶ ሊያናግራቸው መሆኑን ሮይተርስ ታስን ጠቅሶ ዘግቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ እንደገለጸው አምባሳደሯ ከሩሲያው ኮመርሳንት ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሩሲያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቋም አዛብተው ተናግረዋል።
ሚኒስቴር ባለፈው ታህሳስ ወር ስራ የጀመሩት አምባሳደሯ ይህን አስተያየት በመስጠት አጀማመራቸውን አበላሽተዋል ብሏል።
አምባሳደር ሀልፐሪን በዚህ ቃለምልልሳቸው የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሰርጌ ላቭሮቭ የሀሎካስትን ወይም የጀዊሽ የዘርማጥፋትን መዘከር አስፈላጊነት አጣጥለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
አምባሳደሯ በቃ ለምልልሱ ሩሲያ ለፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ የቅርብ ወዳጅ ነችም ብለዋል።
እስራኤል ከዚህ በፊት ከሀማስ ጋር በተያያዘ በእስራኤል የሩሲያ አምባሳደርን ጠርታ ማነጋገሯ ይታወሳል።
እስራኤል የሩሲያን አምባሳደር የጠራችው ሞስኮ በሀማስ ከፍተኛ አመራሮች የተመራ የልኡካን ቡድን ማስተናገዷን ተከትሎ ነበር።
የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ መንስኤ የአሜሪካ የተሳሳተ ፖሊሲ ነው ብላ የምታስበው ሩሲያ፣ በጋዛ ተኩስ እንዲቆም እና ሰላማዊ መፍትሄ እንዲመጣ ትፈልጋለች።
ይህ አቋሟ በእስራኤል በኩል አልተወደደላትም።