የእስራኤል ካቢኔ በሀገሪቱ የሚገኘው የአልጀዚራ ቢሮ እንዲዘጋ ወሰነ
ውሳኔው የቴሌቪዥን ጣቢያው በእስራኤል ስርጭቱን እንዳያስተላልፍ እና የማሰራጫ መሳሪያዎቹ እንዲወረሱ ያደርጋል ተብሏል
እስራኤል አልጀዚራ “የሃማስ አፈቀላጤ ነው፤ የእስራኤልን ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ላይ ጥሏል” የሚል ክስ ታቀርባለች
የእስራኤል ካቢኔ የኳታሩ የቴሌቪዥን ጣቢያ አልጀዚራ ቢሮ እንዲዘጋ ወሰነ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ካቢኔው በእስራኤል የሚገኘው የአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቢሮ እንዲዘጋ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ጠቁሟል።
ከዛሬ ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል የተባለው ውሳኔ የቴሌቪዥን ጣቢያውን የስርጭት ቁሳቁሶች መውረስ እና የተቋሙን ድረገጽ መዝጋት ያካትታል ተብሏል።
እስራኤል ከዚህ ቀደም በጋዜጠኞች ላይ በተናጠል ካሳለፈችው እገዳ ውጭ የውጭ የመገናኛ ብዙሃን እንዲዘጋ ስትወስን አልጀዚራ የመጀመሪያው ይሆናል።
“የአልጀዚራ ጋዜጠኞች የእስራኤልን ብሄራዊ ደህንነት ጎድተዋል፤ በወታደሮች ላይ እርምጃ እኝዲወሰድም ቀስቅሰዋል” የሚለው የኔታንያሁ አስተዳደር፥ የቴሌቪዥን ጣቢያው “የሃማስ አፈቀላጤ” ነው በሚል ይከሳል።
በዶሃ የሚገኘው የአልጀዚራ ዋና ቢሮ ስለእስራኤል ውሳኔ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
ይሁን እንጂ የእገዳ ውሳኔው በፍልስጤም በሚንቀሳቀሱ ጋዜጠኞች ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖረው የአልጀኢራ የአረብኛ ጋዜጠኞች ለአሶሼትድ ፕረስ ተናግረዋል።
የኳታር እና እስራኤል ግንኙነት ከጋዛው ጦርነት ወዲህ እየሻከረ መጥቷል።
ኔታንያሁ የሃማስ መቀመጫ የሆነችው ዶሃ በቡድኑ ላይ ጫና እያደረገች አይደለም የሚል አስተያየት ከሰጡ ወዲህም ግንኙነቱ ይበልጥ መሻከሩ ይታወሳል።
እስራኤል በጋዛ እየፈጸመች ያለውን ድብደባ ለአለማቀፉ ማህበረሰብ በማድረስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ይታወቃል።
በርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያው ጋዜጠኞች እና የካሜራ ባለሙያዎች በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደላቸውም ተደጋግሞ ተገልጿል።
ቴል አቪቭ ግን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዘገባዎች ለሃማስ ወገንተኝነት የሚታይባቸውና የተጋነኑ መሆናቸውን በመግለጽ በሀገሪቱ ስርጭቱን እንዲያቋርጥ ወስናለች።
ሳኡዲ አረቢያ፣ ዮርዳኖስ፣ አረብ ኤምሬትስ እና ባህሬን ከኳታር ጋር ግንኙነታቸውን ሲያቋርጡ አልጀዚራ እንዲዘጋ ማድረጋቸው አይዘነጋም።