ሀማስ የጋዛው የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈርስ አልፈልግም አለ
እስራኤል የስምምነቱን ነጥቦች አላከበረችም በሚል ቡድኑ በመጪው ቅዳሜ የሚደረገውን የታጋቾች ልውውጥ ማገዱ ይታወሳል
ሃማስ ቅዳሜ ታጋቾችን የማይለቅ ከሆነ እስራኤል ዳግም ጦርነት እንደምትጀምር ዝታለች
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ የጋዛው የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈርስ ፍላጎት እንደሌለው ገለጸ፡፡
ቡድኑ በስምምነቱ መሰረት በዚህ ሳምንት ተጨማሪ ሶስት ታጋቾችን ለመልቀቅ ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም እስራኤል የስምምነቱን ነጥቦች ጥሳለች በሚል ታጋቾችን እንደማይለቅ አስታውቋል፡፡
ሀማስ በዛሬው ዕለት ባወጣው አዲስ መግለጫ የስምምነቱ ተግባራዊነት እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳለው ነው የገለጸው፡፡
የቡድኑ ቃል አቀባይ አብደል ላቲፍ አልቃኑዋ “የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲፈርስ ፍላጎት የለንም፤ ስምምነቱንም ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ ነን፤ ነገር ግን እስራኤል ሙሉ በሙሉ የስምምነቱን መርሆዎች እንድትከተል እንፈልጋለን” ብለዋል ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታጣቂ ቡድኑ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ታጋቾችን የማይለቅ ከሆነ “ከፍተኛ ትርምስ” እንደሚፈጠር አስጠንቅቀዋል፡፡
እስራኤል በበኩሏ ጦርነቱን ድጋሚ እንደምታስጀምር ያስጠነቀቀች ሲሆን አሁን የምትከፍተው ውግያ ከዚህ ቀደሙ እንደሚከፋ ነው ያሳሰበችው፡፡
ሀማስ በዛሬው ዕለት በቃል አቀባዩ በኩል ባወጣው መግለጫ "ትራምፕ እና ኔታንያሁ የሚጠቀሙበት የማስፈራሪያ እና የዛቻ ቋንቋ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ አያገለግልም" ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም እስራኤል የሰብዓዊ ህጎችን የምታከብር ከሆነ የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጡን ለማስቀጠል ፈቃደኛ መሆኑን ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡
በጋዛ የሀማስ ሃላፊ ካሊል አልሃያ የተመራ ልዑካን ቡድን ረቡዕ የግብፅን የደህንነት ባለስልጣናትን አግኝቶ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመቅረፍ ውይይት አድርጓል፡፡
ለድርድሩ ቅርበት ያላቸው የፍልስጤም ባለስልጣናት ለሮይተርስ እንደተናገሩት የተኩስ አቁም ስምምነቱ አደራዳሪዎች ግብፅ እና ኳታር በጋዛ ድጋሚ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ መፍትሄ ለማግኘት እየሞከሩ ነው።
እስራኤል በበኩሏ ሀማስ በመጪው ቅዳሜ ታጋቾችን የማይለቅ ከሆነ ዳግም ወረራ ለመጀመር ተጠባባቂ ወታድሮቿ ጦሩን ለመቀላቀል በተጠንቀቅ እንዲጠባበቁ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች፡፡
በሀማስ እና እስራኤል መካከል በተኩስ አቁሙ ስምምነት አፈጻጸም የተነሳ በተፈጠረው ውዝግብ ውጊያ የሚከሰት ከሆነ ትራምፕ ጋዛን ለመቆጣጠር ላስቀመጡት እቅድ መሳካት መልካም አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል ተንታኞች ተናግረዋል፡፡