እስራኤል በ2025 አጋማሽ በኢራን ላይ ጥቃት ልትፈጽም እንደምትችል ተነገረ
የናታንዝ እና ፎርዶው የኒዩክሌር ጣቢያዎችም የጥቃቱ ኢላማ እንደሚሆኑ የአሜሪካ የደህንነት ምንጮች ገልጸዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/13/273-110121-ap20353229237376-640x400_700x400.jpg)
ቴህራን ከጥር ወር ጀምሮ እያካሄደችው ባለው ወታደራዊ ልምምድ ከእስራኤል ለሚቃጣባት ጥቃት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እያደረገች ነው
እስራኤል በ2025 አጋማሽ በኢራን ላይ ጥቃት ልትፈጽም እንደምትችል ተነገረ።
ዋሽንግተን ፖስት የአሜሪካ የደህንነት ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው ጥቃቱ የኢራን የኒዩክሌር ፕሮግራምን የማዳከም አለማ ያለው ነው።
በባይደን አስተዳደር ማብቂያ እና በትራምፕ አስተዳደር ጅማሮ የተሰበሰቡ የደህንነት መረጃዎችን ይህንኑ እንደሚያረጋግጡም ነው የተገለጸው።
የናታንዝ እና ፎርዶው የኒዩክሌር ጣቢያዎችም የእስራኤል ጥቃት ኢላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ መረጃዎቹ ማመላከታቸውን ወልስትሪት ጆርናል አስነብቧል።
ሬውተርስ ግን ዋይትሃውስ በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቆ ማረጋገጫ እንዳልሰጠ ዘግቧል። የእስራኤል መንግስት፣ የአሜሪካ የስለላ ተቋም (ሲአይኤ) እና ሌሎች የደህንነት ተቋማትም ዝምታን መርጠዋል ነው ያለው።
የዋይትሃውስ የብሄራዊ ደህንነት ምክርቤት ቃልአቀባይ ብሪያን ሁግስ፥ ፕሬዝዳንት ትራምፕ "ኢራን የኒዩክሌር የጦር መሳሪያ እንዲኖራት አይፈቅዱም" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ምንም እንኳን የረጅም ጊዜ የሀገራቱን ቁርሾ በንግግር ለመፍታት ቢፈልጉም "ኢራን ስምምነት ላይ ለመድረስ ካልፈለገች እንዲሁ ሊጠብቁ አይችሉም" ሲሉም ለዋሽንግተን ፖስት ተናግረዋል።
እስራኤል በትራምፕ የስልጣን ዘመን በኢራን ላይ ልትፈጽመው የምትችለው ጥቃት የቴህራንን የኒዩክሌር ፕሮግራም በሳምንታት ወይም በወራት እንደሚያጓትት የደህንነት ምንጮቹ ገልጸዋል።
የቴል አቪቭ ጥቃት እና ቴህራን ልትሰጠው የምትችለው አጻፋ የቀጠናውን ውጥረት እንደሚያባብሰውም ይታመናል።
ኢራን ከጥር ወር መጀመሪያ አንስቶ ለሁለት ወራት የሚዘልቅ ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ እያካሄደች ነው፤ አዳዲስ የጦር መርከቦችና ድሮኖችም እያስተዋወቀች ትገኛለች።
ወታደራዊ ልምምዱ ከእስራኤልም ሆነ ከአጋሯ አሜሪካ ሊቃጣ የሚችል ጥቃትን ለመመከት እና አጻፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት እየተደረገበት መሆኑንም ደጋግማ መግለጿ ይታወሳል።