የእስራኤላዊው ቢሊየነር መርከብ በኢራን በድሮን ተመታለች - አሜሪካ
በእቃ ጫኝ መርከቧ ላይ ጉዳት አድርሷል ስለተባለው የድሮን ጥቃት ቴህራን ምላሽ አልሰጠችም
የመርከቧ ባለቤት ኩባንያ ሁሉም የመርከቧ ሰራተኞች ጉዳት እንዳልደረሰባቸውና መርከቧ ጉዞዋን መቀጠሏን አስታውቋል
በህንድ ውቅያኖስ ጉዞ ላይ የነበረች እቃ ጫኝ መርከብ በኢራን የድሮን ጥቃት መመታቷን አሜሪካ አስታወቀች።
አሶሼትድ ፕረስ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአሜሪካ ባለስልጣንን ጠቅሶ እንዳስነበበው፥ ግዙፍ መርከቧ የእስራኤላዊ ቢሊየነር ንብረት ናት።
የማልታ ሰንደቅ አለማ የምታውለበልበው መርከብ ሶስት ማዕዘን ቅርጽ ባላትና ቦምብ በምትሸከም “ሻሄድ - 136 ድሮን” ሳትመታ እንደማትቀርም ነው የተገለጸው።
የፈነዳችው ድሮን በመርከቧ ላይ ጉዳት ማድረሷን የጠቀሱት የአሜሪካ ባለስልጣን፥ ሁሉም የመርከቧ ሰራተኞች ግን ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰባቸው ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከዚህ ጥቃት ጀርባ መኖሩ እንዴት እንደተረጋገጠ ግን አላብራሩም፡፡
አል ማያደን የተሰኘው ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ያለው የቴሌቪዥን ጣቢያ የእስራኤል መርከብ በህንድ ውቅያኖስ ጥቃት እንደደረሰበት ዘግቦ የቴህራን ሚዲያዎችም ምንጭ እያደረጉ ተቀባብለውታል።
መርከቧ በእስራኤላዊ ቢሊየነር የሚተዳደረው “ኢስተርን ፓስፊክ ሺፒንግ” ኩባንያ ንብረት መሆኗ ተጠቁሟል።
ኩባንያው ስለደረሰው ጥቃት ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም መርከቧ ጉዞዋን መቀጠሏን አስታውቋል።
ቴህራንም ከዋሽንግተን ባለስልጣናት ለተነሳው ውንጀላ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም።
ይሁን እንጂ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በኢራን የሚደገፉ ሃይሎች በመርከቦች እና የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።
የየመን ሃውቲ ታጣቂዎች በቅርቡም ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላት ያሏትን መርከብ ማገታቸውን ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው።