በእስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ያደረሰው ሀማስ "ለሁሉም የፖለቲካ ንግግሮች" በሬ ክፍት ነው ብሏል
የሀማስ ከፍተኛ ባለስልጣን ቡድኑ “ዓላማውን በማሳካቱ" ከእስራኤል ጋር ለስምምነት ለመወያየት በሩ ክፍት ነው ብለዋል።
ሙሳ አቡ ማርዙክ ሀማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመወያየት ፈቃደኛ ነው ወይ ተብለው ሲጠየቁ "ለሁሉም የፖለቲካ ንግግሮች" በሩ ክፍት ነው ብለዋል።
ቅዳሜ ዕለት ሀማስ እስራኤል ላይ በአየር፣ በባህርና በምድር ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ እስራኤል ጦርነት አውጃለች።
በእስራኤል-ፍልስጤም ጦርነት የሟቾች ቁጥር ከአንድ ሽህ 100 በላይ ደርሷል።
ጥቃቱን ተከትሎ በጎፈቃደኞች አስከሬንና የተጎዱ ሰዎችን ለመፈለግ ሲዘዋወሩ ታይተዋል።
ሆኖም የሙዚቃ ፌስቲቫል እየተካሄደ ባለበት ቦታ ቢያንስ 260 አስከሬኖች መገኘታቸው አስደንጋጭ ግኝት ሆኖ ተመዝግቧል።
የእስራኤል የነፍስ አድን አገልግሎት በጋዛ አቅራቢያ በሚገኘው ኪቡትዝ ሬኢም በመቶዎች የሚቆጠሩ አስከሬኖችን ማግኘቱን ተናግሯል።
እስራኤል በደቡባዊ ከተሞች ከሀማስ ተዋጊዎች ጋር ተዋግታለች።
ሀገሪቱ በጋዛ ሰርጥ አቅራቢያ በአስር ሽህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን በጅምላ አሰባስባ ከአሜሪካው 9/11 ጋር ተመሳሳይ ነው ለተባው ጥቃት ምላሽ እየሰጠች ነው።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የጋዛ ሲቪሎች ከሀማስ ቦታዎች እንዲርቁ በማስጠንቀቅ አካባቢውን ዶግ አመድ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።