ጥቃቱን ተከትሎ እስራል ጦርነት ውስጥ መግባቷን እና ጋዛ በሚገኙ የሀማስ ቦታዎች ላይ የአየር ጥቃት መሰንዘሯን አስታውቃለች
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ በትናንትናው እለት በእስራኤላ ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት አድርሷል።
ከጋዛ ሰርጥ ሆኖ የሮኬት ጥቃት ያዘነበው ሀማስ በታጣቂዎቹ በመታገዝ ወደ እስራኤል ከተሞች ዘልቆ በመግባት ጭምር ነው ከባድ የተባለውን ጥቃት ያደረሰው።
ጥቃቱን ተከትሎ እስራል ጦርነት ውስጥ መግባቷን እና ጋዛ በሚገኙ የሀማስ ቦታዎች ላይ የአየር ጥቃት መሰንዘሯን አስታውቃለች።
ከአየር ጥቃቱ በተጨማሪ እስራኤል በደቡባዊ እስራኤል ከቡድኑ ታጣቂዎች ጋር እየተዋጋች መሆኑን ገልጻለች።
ስለግጭቱ ዓለም ምን አለ?
ጀርመን
"ከእስራኤል አስደንጋጭ ዜና ደርሶናል። ከጋዛ የተወነጨፈው ሚሳይል እና እየተባባሰ የመጣው ግጭት አስደንግጦናል። ጀርመን ሀማስ ያደረሰውን ጥቃት ታወግዛለች፣ ከእስራኤል ጎንም ትቆማለች" ብለዋል።
ፈረንሳይ
ፕሬዝደንት ማክሮን ሀማስ ያደረሰውን ጥቃት በጽኑ እንደሚያወግዙ ገልጸዋል።
ፕሬዝደንቱ ኤክስ ወይም ቀደም ሲል ትዊተር በሚባለው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ "ለተጎችዎች ያለኝን ሙሉ አጋርነት እገልጻሉሁ" ሲሉ ጹፈዋል።
ሳኡዲ አረቢያ
የሳኡዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ግጭት የገቡት እስራኤል እና ሀማስ አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
"በበርካታ የፍልጤም ቡድኖች እና በእስሬኤል ወራሪ ኃይሎች መካከል የተፈጠረውን እና በበርካታ ቦታዎች ግጭት የፈጠረውን ክስተት እየተከታተልነው ነው።"
ግብጽ
የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የእስራኤል እና ሀማስ ግጭት የሚባባስ ከሆነ ከፍተኛ አደጋ ያስከትላል ሲል አስጠንቅቋል።
ሁለቱም አካላት ግጭቱን ከማባባስ እንዲታቀቡ እና ንጹሃን እንዲጠብቁ ጠይቋል ሚኒስቴሩ።
ዩናይትድ ኪንግደም
የዩናይትድ ኪንግደም(ዩኬ) ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄምስ ክሌቨርይ ሀማስ ያደረሰውን ዘግናኝ ጥቃት እናወግዛለን ብለዋል።
ዩኬ የእስራኤልን ራሷን የመከላከል መብት ትደግፋለች ብለዋል ሚኒስትሩ።
ቱርክ
የቱርኩ ፕሬዝደንት ኤርዶጋን ሁሉም አካላት ግጭት እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
"አባባሽ ከሆኑ ተግባራት መታቀብ አለባቸው"ሲሉ ተናግረዋል ኤርዶጋን።
ኔዘርላንድ
የደች ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩቴ እንዳሉት ሀማስ ስላደረሰው ያልተጠበቀ ጥቃት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ንታንያሁ ጋር ተነጋግረዋል።
ጠቅላይ ማርክ ሩቴ ኔዘርላንድ ጥቃቱን እንደምታወግዝ እና አስራኤልን እንደምትደግፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር ንታንያሁ እንደገለጹላቸው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፈዋል።
ሩሲያ
ሩሲያ በእስራኤል- ፍልስጤም ግጭት ጉዳይ ከአስራኤል፣ ከፍልስጤም እና ከአረብ ሀገራት ጋር ንግግር ማድረጓን ኢንተርፋክስ ኒውስ የሩሲያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚካኤል ቦግዳኖቭን ጠቅሶ ዘግቧል። ምክትል ሚኒስትሩ ሁለቱም አካላት ግጭቱን ከማባባስ እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ዩክሬን
ዩክሬን በእስራኤል ላይ እየተካሄደ ያለውን እና በእየሩሳሌም እና በቴልአቪቭ ከተሞች ንጹሃንን ለጥቃት የዳረገውን "የሽብር ጥቃት" ታወግዛለች ብሏል የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።
"እስራኤል ራሷን ከጥቃት ለመከላከል ያላትን መብት እንደግፉለን"።
ፖላንድ
የፖላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዚብግነው ራዩ ኤክስ ላይ "ሀማስ እያደረገ ያለውን ጥቃት በጽኑ አወግዛለሁ። ይህ ምክንያት የለሽ ወረራ እና ጥቃት ተቀባይነት የለውም።" ብለዋል።
ቸክ ሪፐብሊክ
የቸክ ፕሬዝደንት ፒተር ፖቬል ባወጡት መግለጫ በእስራኤል እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከጋዛ የተወነጨፈው ሮኬት የሽብር ድርጊት ነው ሲሉ ገልጸውታል።
የሀማስ ኮማንዶዎች የእስራኤልን ድንበር ጥሰው ጥቃት መፈጸማቸው የእስራኤልን እና ፍልስጤምን ግጭት በንግግር ለመፍታት ያደናቅፋል ብለዋል።
ግጭቱ በመቀስቀሱ ምክንያት ንታንያሁ የእራኤል የረጅም ጊዜ አጋር ወደ ሆነችው ቼክ ሪፐብሊክ የሚያደርጉትን ጉዞ ለማራዘም ተገደዋል።
አውስትራሊያ
የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ሻለንበርግ ሀማስ በእስራኤል ላይ ያደረሰውን "የፈሪ" ጥቃት አውግዋል። ይህ ጥቃት በቅርብ አመታት ውስጥ ከታየው የተለየ ነው ያሉት ሚኒርትሩ እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት አላት ብለዋል።
ጣሊያን
የጣሊያ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እንደገለጸው የጣሊያን መንግስት እየተፈጸመ ያለውን ዘግናኝ ጥቃት በቅርበት እየተከታተለው ነው። ጥቃቱን ያወገዘው መንግስት እስራኤል ራሷን ለመከለከል የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ ገልጿል።
ስዊድን
የስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግጭቱ እንዲቆም እና ንጹሃን እንዳይጎዱ ጥሪ አቅርቧል።
አሜሪካ
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሀማስ ያደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል። ፕሬዝደንቱ እንደተናገሩት አሜሪካ፣ እራኤል የተቃጣበትን የሽብር ጥቃት ለመቀልበስ የምትፈልገው ሁሉ እንዲኖራት ታደርጋለች ብለዋል።
እየተካሄደ ባለው ግጭት ዙሪያ፣ ከእራኤል ጋር የዲፕሎማት ለዲፕሎማት፣ የደህንነት ለደህንነት እና የወታደራዊ ለወታደራዊ ተቋማት ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ፕሬዝደንቱ ባይደን ገልጸዋል።