ትራምፕ ለሃማስ "የመጨረሻ" ነው ያሉትን ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ
በጋዛ የሚገኙት ታጋቾች ሙሉ በሙሉ ካልተለቀቁ "የሃማስ ፍጻሜ ይሆናል፤ የጋዛ ነዋሪዎችም ከፍተኛ ዋጋ ትከፍላላችሁ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል

የትራምፕ ዛቻ እስራኤል በጋዛ ዳግም ጦርነት እንድትጀምር ፈቃደኝነታቸውን ያሳዩበት ነው ተብሏል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለፍልስጤሙ ሃማስ የመጨረሻ ነው ያሉትን ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።
ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ሶሻል ማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ዘለግ ያለ መልዕክት ሃማስ ሁለት ምርጫ እንዳለው ጠቁመዋል፤ ሁሉንም በጋዛ የሚገኙ ታጋቾች (ህይወታቸው ያለፈውን ጭምር) መልቀቅ አልያም "መጥፋት"።
"ሁሉንም ታጋቾች አሁኑኑ ልቀቁ፤ በሌላ ጊዜ አይደለም፤ የገደላችኋቸውን ታጋቾች አስከሬንም በፍጥነት መልሱ፤ ይህ ካልሆነ ግን ያከትምላችኋል" ነው ያሉት።
ትራምፕ በቅርቡ በእስራኤልና ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት የተለቀቁ ስምንት ታጋቾችን ትናንት በዋይትሃውስ አግኝተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከታጋቾቹ ጋር ከተገናኙ ከጥቂት ስአታት በኋላም ዋይትሃውስ ከሃማስ ጋር አሜሪካዊ ታጋቾች በሚለቀቁበት ሁኔታ በቀጥታ መምከሩን አረጋግጧል።
የትራምፕ ማስጠንቀቂያ እስራኤል በጋዛ ዳግም ጦርነት እንድትጀምር ፈቃዳቸውን ያሳዩበት ነው ተብሏል።
"እስራኤል ስራዋን እንድታጠናቀቅ የፈለገችውን ሁሉ እየላኩላት ነው፤ የምለውን ካልፈጸማችሁ የትኛውም የሃማስ አባል ደህንነቱ አደጋ ላይ ነው" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
የፍልስጤሙ ቡድን ተዋጊዎች ከጋዛ ለቀው በመውጣት ራሳቸውን የማትረፍ እድል እንዳላቸውም ነው "የመጨረሻ" ባሉት የማሳሰቢያ መልዕክታቸው ላይ ያሰፈሩት።
የ78 አመቱ ፕሬዝዳንት ለጋዛ ነዋሪዎችም ተመሳሳይ መልዕክት ልከዋል። "የጋዛ ህዝቦች ውብ መጻኢ ከፊታችሁ አለ፤ ግን ታጋቾችን ይዛችሁ አይደለም ይህን የምታዩት፤ ይህን የምታደርጉ ከሆነ (ታጋቾችን) ሟች ናችሁ፤ የብልህ ውሳኔ ወስኑ፤ ሁሉንም ታጋቾች ልቀቁ፤ ካልሆነ ግን ከባድ ዋጋ ትከፍላላችሁ" ብለዋል።
ትራምፕ ለሃማስም ሆነ ለጋዛ ነዋሪዎች ያስተላለፉት ተመሳሳይ መልዕክት ሰርጡን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው ለማልማት ለያዙት እቅድ ተፈጻሚነት ቁርጠኛ መሆናቸውን ለማመላከት ነው።
ግብጽ የትራምፕን የጋዛ እቅድ የሚተካና ፍልስጤማውያን ከመሬታቸው እንዳይፈናቀሉ የሚያደርግ እቅድ አቅርባ በአረብ ሀገራት ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወሳል።
የትራምፕ አስተዳደር በካይሮ የቀረበው እቅድ "ጋዛ በአሁኑ ጊዜ ለመኖሪያነት አመቺ አለመሆኗን እንዲሁም ነዋሪዎቿ በፍርስራሾች እና ባልተፈነዱ ፈንጂዎች ውስጥ መኖር አይችሉም የሚለውን እውነታ አልተመለከተም" በማለት አጣጥሎታል።
እስራኤልም እቅዱ “መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ” ነው በሚል ውድቅ ማድረጓ አይዘነጋም።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ሃማስ እና ፍልስጤማውያንን በእኩል ተመልክተው ያስተላለፉት ማሳሰቢያ ከ48 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው የጋዛ ጦርነት ዳግም መቀስቀሱ እንደማይቀር አመላካች ነው ተብሏል።
እስራኤልና ሃማስ ባለፈው ሳምንት የተጠናቀቀውን የመጀመሪያ ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማስቀጠል አለመቻላቸውም ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።