ትራምፕ በንግግራቸው ወቅት አዘውትረው ከሚጠቀሟቸው የእጅ አገላላጾች ጀርባ ያለው መልዕክት ምንድን ነው?
ትራምፕ በእጃቸው ሶስት ማዕዘን ቅርጽ እና ቡጢ እየጨበጡ በተደጋጋሚ የሚያሳዩዋቸው ምልክቶች ከተራ የእጅ አገላላጸ ያለፈ ትርጉም እንዳለው ባለሙያዎች ተናግረዋል

ትራምፕ ባሳለፍነው ማክሰኞ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት ክብረ ወሰን የሰበረ ረጅም ንግግር እነዚህን የእጅ አገላለጾች በስፋት ተጠቅመዋቸዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት የሚያሳዩዋቸው የእጅ አገላላጾች የታዳሚያንን እና የአለምን ህዝብ ትኩረት ከመሳብ ያለፈ ትርጉም እንዳላቸው ከሰሞኑ በስፋት እየተዘገበ ነው፡፡
ትራምፕ በድፍረት ከተሞሉ ፖሊሲወቻቸው እና አወዛጋቢ ከሆኑ የአስፈፃሚ ውሳኔዎቻቸው ባለፈ በእጃቸው በሚያደርጉት ትኩረት በሚስቡ እንቅስቃሴዎች የብዙዎችን ቀልብ እየሳቡ ነው።
በሁለተኛው የስልጣን ዘመናቸው ሀላፊነት ከያዙ 6 ሳምንታት ያስቆጠሩት ፕሬዝዳንቱ ባሳለፍነው ማክሰኞ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት ክብረወሰን የሰበረ ንግግር እነኚህን ምልክቶች በስፋት ሲጠቀሙ ታይተዋል፡፡
ጋዜጣው በቅርቡ በቲክቶክ ማህበራዊ ትስስር ገጽ በሰፊው እየተዘዋወረ የሚገኘው ትራምፕ በተደጋጋሚ የሚያሳዩት የሶስት ማዕዘን ቅርጽ ያለው የእጅ ምልክት ሆን ተብሎ እንደሚደረግ እና የተለየ ምልዕክት እንዳለው አስነብቧል፡፡
በቲክቶክ ላይ ስለ እጅ አቀማማጡ ትንታኔ ከሰጡ ሰዎች መካከል አንዱ፤ የእጅ ምልክቱ ሀብታም ሰዎች ቀደም ብለው የሚማሩት እና የሀይል እና የስልጣን ማሳያ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ሌላ የማህበራዊ ሚድያው ተጠቃሚ ደግሞ አዕምሮን ሚዛናዊ ለማድረግ ፣ ጭንቀትን ለማርገብ እና ትኩረት ለማድረግ ሰዎች እንደሚጠቀሙት ተናግሯል፡፡
ሌላው ትራምፕ በተደጋጋሚ የሚጠቀሙት የእጅ አገላላጽ የቡጢ ምልክት የሚያሳዩበት ሲሆን ይህም የሀያልነት እና የእችላለሁ፣ ነገሮችን ለመፈጸም ሙሉ አቅም አለኝ እንዲሁም የአቅም ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድ ተዘግቧል፡፡
የትራምፕን የእጅ እንቅስቃሴ ትርጓሜ በተመለከተ የተለያዩ ንድፈ ሐሳቦች ቢኖሩም እውነተኛ ትርጉሙ የክርክር እና የመላምት መወዛገቢያ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
የእጅ አገላላጽ እና የምልክት ቋንቋ ባለሙያዎች በበኩላቸው ብዙ ጊዜ በራስ የመተማመን ስሜት ለማሳየት ፣ በነገሮች ላይ ሙሉ ቁጥጥር እንዳለ ለመግለጽ ፣ በተለይም አንድ ሰው እያወራበት የሚገኘውን ርዕሰ ጉዳይ በደንብ መረዳቱን ለማሳየት እና በጉዳዩ ላይ ያለውን ጠንካራ አቋም እና ስልጣን ለማንጸባረቅ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
የምልክት ቋንቋ እና የሰወነት እንቅስቃሴ መልዕክት ተንታኞች በተለይ ከፍተኛ የሀገር መሪዎች እና ትላልቅ የቢዝነስ ሰዎች በቃላቸው ከሚናገሯቸው ንግግሮች ባለፈ በሰውነት እንቅስቃሴ በርካታ ድብቅ ምዕክቶችን እንደሚያስተላልፉ ይናገራሉ፡፡
ተቃውሞ ፣ ድጋፍ ፣ በራስ መተማመን ፣ የስልጣን እና የበላይነት ስሜት እንዲሁም ሌሎችም አጀንዳዎችን ለማስተላለፍ ሰዎች በቃላቸው ከሚናገሯቸው በላይ አልያም ንግግራቸውን ይበልጥ ትኩረት ለመስጠት የቅንድብ ፣ የፊት እና የእጅ እንቅስቃሴን በስፋት ይጠቀማሉ፡፡
እነዚህ ምልክቶች ለብዙሀኑ የልማድ ጉዳይ ተደርገው ወይም እንደዘበት የተደረጉ እንቅስቃሴዎች መስለው ቢታዩም ከንግግር ያልተናነስ መልዕክት እንደሚተላለፍባቸው ነው ባለሙያዎቹ የሚናገሩት፡፡