ቴህራን የምትደግፋቸው ቡድኖች በኢራቅና ሶሪያ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ይታወሳል
አሜሪካ በሁለት ሳምንት ውስጥ ሁለተኛውን የአየር ጥቃት በሶሪያ ላይ ፈጽማለች።
በዴር አል ዞር ግዛት ውስጥ የሚገኙ የኢራን አብዮታዊ ዘብ እና አጋሮቹን ወታደራዊ ይዞታዎች ናቸው በሁለት ኤፍ - 15 ጄቶች የተደበደቡት።
የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ሊዮድ ኦስቲን እንዳስታወቁት በምስራቃዊ ሶሪያ የሚገኙ የኢራን እና የምታስታጥቃቸው ቡድኖች የጦር መሳሪያ ማከማቻዎች ተመተዋል።
የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው በኢራቅና ሶሪያ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ለተፈጸሙት ጥቃቶች የአጻፋ ምላሽ ለመስጠት ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በኢራቅና ሶሪያ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ጣቢያዎች ከ40 ያላነሱ ጥቃቶች ተሰንዝረውባቸዋል። በዚህም በጥቂቱ 45 ወታደሮች መቁሰላቸውን ነው ፔንታጎን ያስታወቀው።
“ኢራን የምትደግፋቸው ታጣቂዎች በአሜሪካ ወታደሮች ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት ካልቆመ ተጨማሪ እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉም ሊዩድ ኦስቲን አስጠንቅቀዋል።
ዋሽንግተን በሶሪያ ዴር አል ዞር ግዛት በፈጸመችው የአየር ድብደባ የደረሰው ውድመት በግልጽ አልተነገረም።
ሬውተርስ በንጹሃን ላይ ጉዳት አለመድረሱን አንድ ከፍተኛ የሀገሪቱ ወታደራዊ አዛዥ ነገሩኝ ቢልም የምርመራ ስራው ተጠናቆ ይፋ አልሆነም።
በሶሪያ 900 በኢራቅ ደግሞ 2 ሺህ 500 ወታደሮች ያሏት አሜሪካ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ወደ ቀጠናው እንዳይስፋፋ በሚል ተጨማሪ ወታደሮች እና የጦር መርከቦችን ልካለች።
ለሃማስ ድጋፍ የምታደርገው ኢራንም የዋሽንግተን እርምጃ ጦርነቱን ይበልጥ እንደሚያባብሰው በመግለጽ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።
በኢራቅና ሶሪያ ባሉ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ የተፈጸሙት ጥቃቶችም የዚህ ማስጠንቀቂያዋ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
በቴህራን የሚደገፉት የየመን ሃውቲ ታጣቂዎች በትናንትናው እለት የአሜሪካ ድሮንን መትተው መጣላቸውም ሌላኛው የጦርነቱ አድማስ እየሰፋ መሄድን አመላካች ነው ተብሏል።