የእስራኤል እና የፍልስጤም ሃማስ ጦርነት፤ ምን አዳዲስ ነገሮች ተከስተዋል?
እስራኤል የጋዛ ኢላማዎች ላይ የአየር ድብደባ ፈጽማለች፤ ሃማስ ወደ እስራኤል ሮኬት መተኮሱን ቀጥሏል
በእስራኤል 1300 ሰዎች በጋዛ ደግሞ 1200 ፍልስጤማውያን እስካሁን በጦርነቱ ሞተዋል
ሃማስ ባሳለፍነው ቅዳሜ በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ እና ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል የተጀመረው ጦርነት ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን ይዟል።
በሃማስ ጥቃት እና በእስራኤል የአየር ድብደባ ከሁለቱም ወገኖች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ2 ሺህ 500 ማለፉ ተነግሯል።
የእስራኤል መከላከከያ ኃይል ባወጣው መረጃ መሰረት በሃማስ ጥቃት የሞቱ እስራኤላውን ቁጥር 1300 የደረሰ ሲሆን፤ ከ3 ሺህ 300 በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
አሜሪካ በሃማስ ጥቃት የተገደሉ ዜጎቿ ብዛት 22 መድረሱን አስታውቃለች።
ታይላንድም በሃማስ ጥቃት በእስራዔል ውስጥ የተገደሉባት ዜጎቿ ቁጥር 21 መድረሱን ገልጻለች።
የፍልስጤም ባለስልጣናት በሰጡት መረጃ ደግሞ በእስራኤል የአየር ድብደባ የሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር 1 ሺህ 200 መድረሱን የገለጹ ሲሆን፤ 5 ሺህ 600 ሰዎች ቆስለዋል።
የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ በእስራኤል የአየር ድብደባ 338 ሺህ ሰዎች ከጋዛ መፈናቀላቸውን አስታውቋል።
እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን የአየር ድብደባ ቀጥላለች፤ እስራኤል በአንድ ሌሊት በጋዛ የሚገኙ 200 ኢላማዎች መትታለች።
የእስራኤል ጦር የአየር ድብደባዎቹ የሃማስን ዋሻዎች እና ቤትዎርኮችን ኢላማ ያደረጉ መሆኑን አስታውቋል።
እስራኤል ከአየር ድብደባ በተጨማሪ በምድር ውጊያ ለማካሄድ 300 ሺህ ወታደሮቿን ወደ ጋዛ ድንበር አስጠግታለች።
እስራኤል በትናትናው እለት አዲስ “የጦርነት ጊዜ ካቢኔ" አዋቅራለች፤ ኮሚቴው ውስጥ ታዋቂው የተቃዋሚ መሪ ቤኑ ጋንዝ ተካተዋል።
ሃማስ ወደ እስራኤል የተለያዩ ክፍሎች ሮኬት መተኮሱን አሁንም ቀጥሎበታል።
እስራኤል እግረኛ ጦሯን ወደ ድንበር ማስጠጋቷን ተከትሎም፤ ሀማስ "የሚያስፈራን ነገር የለም"የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
የቀድሞው የሀማስ ኃላፊ ካሊድ ማሻል ጎረቤት ሀገራት እየተደረገ ባለው የጸረ- እስራኤል ውጊያ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ማሻል የጆርዳን፣ የሶሪያ፣ የሊባኖስ እና የግብጽ ህዝብና መንግስታት ፍልስጤማውያንን የመርዳት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
የሃማስ ቃል አቀባይ ካሊድ ካዶሚ በበኩሉ፤ ቡድኑ በእስራኤል ላይ የጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ ባለፉት አስርት ዓመታት ፍልስጤማውያን ላይ ለተፈጸመው ግፍ ምላሽ ነው ብሏል።
“ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በጋዛ የሚፈጸመውን ግፍ እንዲያስቆም እንፈልጋለን” ያለው ቃል አቀባዩ፤ “አል ኣቀሳን ጨምሮ ቅዱሳን ስፍራዎቻችን ለዘመቻው መጀመር መነሻ ነው” ብሏል።
መሳሪያ የታጠቀ ማንኛውም ፍልስጤማዊ ጦርነቱን እንዲቀላቀል ጥሪ ያቀረበው ሃማስ፤ የዌስት ባንክ ታጣቂዎች፣ የአረብ ማህበረሰብ እና ሙስሊም ሀገራት ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ በቴሌግራም በለቀቀው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል።