የፍልስጤሙ ሃማስ ሶስት እስራኤላውያን ታጋቾችን ለቀቀ
እስራኤል በምትኩ 183 የእድሜ ልክ እና ረጅም አመት እስራት የተላለፈባቸውን ፍልስጤማውያን እስረኞች ፈታለች

እስራኤልና ሃማስ በሁለተኛው ምዕራፍ የጋዛ ተኩስ አቁም በዶሃ ሊያደርጉት የነበረው ድርድር በትራምፕ ጋዛን የመጠቅለል እቅድ ተጓቷል
የፍልስጤሙ ሃማስ ዛሬ ሶስት እስራኤላውያን ታጋቾችን ለቋል።
ዛሬ የተለቀቁት ወንድ ታጋቾች ኢሊ ሻራቢ፣ ኦሃድ ቤን እና ኦአር ሌቪ የተባሉ ሲቪሎች ናቸው።
ታጋቾቹ ከዴር አል ባላህ በቀይ መስቀል ተሽከርካሪዎች ተሳፍረው እስራኤል ገብተዋል።
እስራኤል በምትኩ 183 ፍልስጤማውያን እስረኞች መፍታቷን አስታውቃለች።
አምስተኛው ዙር የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ ከጋዛ የሚለቀቁ ታጋቾችን ቁጥር 21 ያደረሰው ሲሆን ቀሪ ሰባት ታጋቾች በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት እንደሚለቀቁ ይጠበቃል።
እስራኤል በአራት ዙሮች 383 ፍልስጤማውያን እስረኞችን መፍታቷን ያስታወሰው ሬውተርስ፥ ዛሬ ከተፈቱት 183 እስረኞች ውስጥ ከ70 በላዩ የእድሜ ልክ እና ረጅም አመታት እስራት የተፈረደባቸው ናቸው ብሏል።
ሃማስ የሚለቀቁትን ታጋቾች ስም ዝርዝር ይፋ ከማድረጉ ከስአታት በፊት እስራኤል በስምምነቱ መሰረት ወደ ጋዛ በቂ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲገባ አልፈቀደችም ሲል ወቅሷል። የተኩስ አቁም ስምምነቱ ወደ ጋዛ 600 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መግባት እንዳለባቸው ያመላክታል።
በጋዛ የሚገኘው የሃማስ ሚዲያ ቢሮ ሃላፊ ሳላማ ማሩፍ፥ የተኩስ አቁም ስምምነቱ መተግበር ከጀመረ ወዲህ 12 ሺህ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ መግባት ቢኖርባቸውም የገቡት 8 ሺህ 500 ብቻ ናቸው ብለዋል።
የህክምና እና መጠለያ ቁሳቁሶችም ሆን ተብሎ ወደ ጋዛ እንዳይገቡ ተደርጓል ሲሉም ወቅሰዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ (ኦቻ) ሃላፊ ቶም ፍሌቸር ግን ከተኩስ አቁሙ ወዲህ ምግብ፣ መድሃኒት እና ድንኳኖች የጫኑ 10 ሺህ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ መግባታቸውን ተናግረዋል።
እስራኤልና ሃማስ በአሜሪካ፣ ኳታርና ግብጽ አደራዳሪነት የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት በሶስት ምዕራፎች የሚተገበር መሆኑ ይታወሳል።
በፈረንጆቹ ጥር 19 2025 ተግባራዊ መሆን የጀመረው የመጀመሪያው ምዕራፍ የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ ሊጠናቀቅ ሁለት ሳምንታት ቀርተውታል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ በኳታር ሊካሄድ የነበረው ድርድር የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ አሜሪካ በማቅናታቸው ተጓቷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋዛን የመጠቅለል እቅድም በድርድሩ ላይ ጥቁር አሻራ እንደሚያሳርፍ እየተነገረ ነው።