ኔታንያሁ የትራምፕን ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማስወጣት እቅድ አወደሱ
ትራምፕ ወደ ጋዛ የአሜሪካ ወታደሮችን እንደሚልኩ እንዳልተናገሩና የእቅዳቸው ዋና ትኩረት ጋዛን መልሶ መገንባት መሆኑንም ገልጸዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/06/273-105315-netanyahu_700x400.jpg)
ዋይትሃውስ አለማቀፍ ውግዘቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የሚወጡት "በጊዜያዊነት" ነው ብሏል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋዛን ለመቆጣጠር ያቀረቡት ሃሳብ የሚደነቅ ነው አሉ።
ኔታንያሁ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የትራምፕን እቅድ ዝርዝር ጉዳዮች ከመናገር ቢቆጠቡም "ስህተቱ ምንድን ነው?" ሲሉ ጠይቀዋል።
"ከጋዛ መውጣት የሚፈልጉት ወጥተው ጋዛ ዳግም ተገንብታ ቢመለሱ ምን ችግር አለው?" ያሉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ፥ ትራምፕ የአሜሪካ ወታደሮችን ወደ ጋዛ በመላክ ከሃማስ ጋር ጦርነት ለመክፈት ስለማቀዳቸው ጠቁመዋል ብለው እንደማያምኑ አብራርተዋል።
የትራምፕ የጋዛ እቅድ "ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት መልካም ሃሳብ ነው፤ የሁሉንም መጻኢ የተለየ ስለሚያደርግ ተፈጻሚ ቢሆን ባይ ነኝ" ሲሉም አክለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ወደ ዋይትሃውስ እንደገቡ የጋዛ ፍርስራሽ እስኪጸዳ ድረስ ፍልስጤማውያን እንደ ግብጽ እና ዮርዳኖስ ባሉ ሀገራት እንዲጠለሉ ሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ካይሮና አማን እቅዱን ውድቅ ያደረጉት ሲሆን፥ የፍልስጤም እና የአረብ መሪዎችም አጥብቀው ተቃውመውታል።
ትራምፕ በዋይትሃውስ ከኔታንያሁ ጋር ሲመክሩ ጋዛን የመቆጣጠር እቅድ እንዳላቸው መናገራቸውም በበርካታ ሀገራት መሪዎች እና አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ውግዘት ገጥሞታል።
የዋይትሃውስ ቃል አቀባይ ካሮሊን ሊቭት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሜሪካ በጋዛ ወታደሮቿን የማሰማራት እቅድ የላትም ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያቀረቡት እቅድ ፍልስጤማውያንን በጊዜያዊነት ከቀያቸው የማስወጣትና የመልሶ ግንባታ ስራው ሲጠናቀቅ ወደ መመለስ መሆኑንም ነው ያነሱት።
አሜሪካ የጋዛ መልሶ ግንባታን ከአጋር ሀገራት ጋር እንጂ ብቻዋን እንደማታከናውንም አብራርተዋል።
የአሜሪካ አጋር እስራኤል በጋዛ ላለፉት 16 ወራት በፈጸመችው ድብደባ ከ47 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለው ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑት ቆስለዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም ባደረገው ምርመራ የጋዛ 69 በመቶ ቤቶችና ህንጻዎች ወድመዋል አልያም ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል ድምዳሜ ላይ መድረሱን ሬውተስ ዘግቧል።
ከ245 ሺህ በላይ ቤቶች የፈራረሱባትን ጋዛ መልሶ ለመገንባት በጥቂቱ 15 አመታት ሊፈጅ ይቻላል መባሉም ይታወሳል።
የትራምፕ እቅድም በጋዛ መልሶ ግንባታ ሰበብ ፍልስጤማውያንን ሀገር አልባ የማድረግ አላማ ያለው ነው የሚሉ ፍልስጤማውያን ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው።