“የግልበጣ ሙከራው በጦር ኃይሉ የውስጥ እና የውጭ አካላት የተቀናበረ ነው”- ጠ/ሚ አብደላ ሃምዶክ
እውነታውን ለህዝብ እናሳውቃለን የድርጊቱ ፈጻሚዎችም በህግ ይጠየቃሉ ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙከራው የሽግግሩ ሁኔታ በግልጽ መገመገም እንዳለበት ያመላከተ እንደሆነም ነው ያስታወቁት
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው በጦር ኃይሉ የውስጥ እና የውጭ አካላት የተቀናበረ ነው ሲሉ ተናገሩ፡፡
ሃምዶክ “የሽግግር ሂደቱን ለመጠበቅ አፋጣኝ እርምጃዎችን እንወስዳለን፤ የሽግግር መንግስቱም ሊጠበቅ ይገባዋል”ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በሃገሪቱ ካገጠሙ ሁነቶች ይልቅ የህዝቡ ቁርጠኝነት ጠንካራ ስለመሆኑም ነው ሃምዶክ የተናገሩት፡፡
የነጻነት እና አብዮት ኃይሎች ለዴሞክራሲያዊው የሲቪሊያን ሽግግሩ ዋስትና ናቸውም ብለዋል፡፡
ሙከራው ትምህርት የተገኘበት እና ነገሮችን በቅርበት ለመከታተል የሚያስችል ከባድ አቋም ለመያዝ ያስቻለ ነው ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡
የሽግግሩ ሁኔታ በግልጽ መገመገም እንዳለበት ማመላከቱንም ጠቁመዋል፡፡
ሃምዶክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙከራውን ሲፈጽሙ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን በማስታወስ እውነታው ለሱዳንና ለዓለም ህዝብ እንደሚገለጽ እና በሙከራው የተሳተፉ አካላት በህግ እንደሚጠየቁ አስታውቀዋል፡፡
ሱዳን ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ/ም ማለዳ ላይ የተጀመረው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ከሽፎ በሙከራው ተሳታፊዎች ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታውቃለች፡፡
ካርቱም ሙከራው ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ነው ከሰዓታት በፊት የገለጸችው፡፡
ይህንንም የሃገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የሚዲያ ጉዳዮች አማካሪ ብ/ጄ አጧሂር አቡ ሃጃ ለሃገሪቱ ዜና አገልግሎት (ሱና) አስታውቀዋል፡፡
ሙከራው በደቡባዊ ካርቱም እና በሰሜናዊ ኦምዱርማን ዋዲ ሲድና ከሚገኘው የሃገሪቱ ጦር ቤዝ በተውጣጡ ሁለት ወታደራዊ ቡድኖች የተደረገ ነው እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ፡፡
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው በሜ/ጄ አብደል ባቂ በክራዊ የተመራ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በሜ/ጄ አብደል ባቂ በክራዊ የሚመሩትና የግልበጣ ሙከራው አካል የሆኑ ወታደሮች በምስራቃዊ ሱዳን የሚገኘውን የሃገሪቱን ጦር ተቆጣጥረው ነበር፡፡
ወታደሮቹ ድልድዮችን መተላለፊያ መንገዶችን ይዘው እንደነበር የተገለጸም ሲሆን የሃገሪቱን ብሔራዊ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያን ለመቆጣጠር በሙከራ ላይ እንደነበሩም ተገልጿል፡፡