ሱዳን የመከፋፈል አደጋ እንደተጋረጠባት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብዳላ ሀምዶክ በተንቀሳቃሽ መልዕክት እንዳሉት፤ሱዳን አሁን ላይ አስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ቀናት ሱዳን የጸጥታ መደፍረስና መበላሸት እንዳጋጠማት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እውነታው ሀገሪቱ የመከፋፈል አደጋ ውስጥ መግባቷን ያሳያል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ሀሳብን የመግለጽ እንቅስቃሴዎች ወደ ዝርፊያና ማስፈራራት መለወጣቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በመልእክታቸው አስታውቀዋል፡፡ ቀጥተኛ ጥቃቶች፣ ግድያዎች በሀገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ መባባሳቸውንም ነው የገለጹት፡፡
በሴቶች ላይም ጥቃት እየደረሰ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጥ እንዲመጣ ያደረጉ ኃይሎች አሁን ላይ በሀገሪቱ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ሊገነዘቡ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ሁሉም የሀገሪቱ ጸጥታ እንዲስተካከልና ወደነበረበት እንዲመለስ ማድረግ እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፈረንጆቹ ሰኔ ሶስት ቀን 2021 ዜጎች በሰለጠነ መንገድ ሃሳባቸውን ቢገልጹም የቀድሞው አስተዳደር ወኪሎች አጋጣሚውን በመጠቀም ለብጥብጥ እንደተጠቀሙበት ገልጸዋል፡፡ የሱዳንን ሉአላዊ የሽግግር መንግስት በሚመራው አልቡርሃንና በጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ መካከል ከፍተኛ ልዩነት እንዳላቸው ይነገራል፡፡